MEDECINS SANS FRONTIERES BELGIUM (MSF BELGIUM) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ያከናወናቸውን ተግባራት በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የተመራ ልዑካን ቡድን ተመልክቷል፡፡
MEDECINS SANS FRONTIERES BELGIUM (MSF BELGIUM) በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቤንች ሸኮ ዞን ያከናወናቸውን ተግባራት በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የተመራ ልዑካን ቡድን ተመልክቷል፡፡
MSF እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ1971 የተመሰረተ ሲሆን በኢትዮጵያ በ1985 በሃገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ስራ መጀመሩን የድርጅቱ የሃገር ተወካይ ረዳት አቶ ፈረዝጊ አሰፋ አብራርተዋል፡፡
ድርጅቱ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለሚከሰቱ አደጋዎች በጤና ዘርፍ ላይ ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመ የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት መሆኑን አክለው በመግለጽ አሁን ላይ በሃገራችን ኮረም ፕሮጀት፣አፋር ፕሮጀክት እና Mobile Ethiopia Emergency team (MEET) የተባሉ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
Mobile Ethiopia Emergency team ፕሮጀክት በፈረንጆች አቆጣጠር 2025 ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመፈራረም ስራ የጀመረ ሲሆን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ በደረሰባቸው የተለያዩ የሃገሪቱ ሰባት አከባቢዎች ላይ ምላሽ የመስጠት ስራ መስራታቸውን እና ከሰባቱ ምላሾች መካከል በልዑካን ቡድኑ የተጎበኘው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ቤንች ሸኮ ዞን የወባ ህክምና ተጠቃሽ መሆኑን ተወካዩ አብራርተዋል፡፡


ድርጅቱ በዞኑ ከሚዛን አማን ሆስፒታል እና ከአስራ ሁለት ጤና ተቋማት ጋር የተንቀሳቃሽ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸው በዚህም ከአስራ ሶስት ሺህ በላይ ሰዎችን ምርመራ በማድረግ 8597 በወባ ወረርሽኝ የተያዙ ሰዎችን የህክምና አገለግሎት እንዲያገኙ መደረጉን አከለው አብራርተዋል፡፡
የሚዛን ቴፒ ዩኒቨርስቲ ህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ማስተባበሪያ ሆስፒታል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እርቅይሁን ጳውሎስ እንዳብራሩት በአከባቢው ከድርጅቱ ጋር በጋራ ከመስራታቸው በፊት በርካታ ችግሮች ይገጥማቸው እንደነበር ገልጸው MSF BELGIUM ጋር በቅንጅት በመስራታቸው በሆስፒታሉ ላይ ያለው ጫና መቀነሱን፣ያጋጥሙ የነበሩ የመድሃኒት እጥረት መሻሻሉን እና በሞባይል ክሊኒክ አገልግሎት ማህበረሰቡ በያለበት አገልግሎት ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል፡፡
አያይዘውም ድርጅቱ በፕሮጀክቱ ሲገለገልበት የነበረውን የህክምና ቁሳቁስ ለሆስፒታሉ አገልግሎት እንዲውል መስጠቱን እና የእውቀት ሽግግር መደረጉን አብራርተው ለሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት እና ለድርጅቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ 1113/2011 የተሰጠውን ተግባርና ሃላፊነት ለመወጣት የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋመ መሆኑን ገልጸው ከዚህ መካከል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የመመዝገብ፣የመከታተልና የመቆጣጠር ስልጣን የተሰጠው በመሆኑ በዚሁ መሰረት ድርጅቱን ለመመልከት መገኘታቸውን አብራርተዋል፡፡
ድርጅቶች ሲቋቋሙ ማህበረሰብን ለማገልገል መሆኑን ገልጸው ባለስልጣን መስሪያቤቱም MSF BELGIUM ባስቀመጠው ዓላማ መሰረት መስራቱን ለማረጋገጥ ባደረግነው ጉብኝት ከሆስፒታሉ አመራርና ሰራተኞች ባገኘነው ምስክርነት በወባ ወረርሽኝ ህክምና ላይ የሰራው ስራ አበረታች መሆኑን ለመገንዘብ ችለናል ብለዋል፡፡
ሁላችንም ለአንድ ሃገር እንደመስራታችን በትብብርና በቅንጅት እንዲሁም የማህበረሰብ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ያደረገ ተግባር መፈጸም ይገባናል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

