የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር "The Emergence of Social Enterprise in Ethiopia: Opportunities, Challenges and Policy Options" በሚል ርእስ የተዘጋጀ የጥናት መነሻ ሃሳብ (Concept Note) ቀርቦ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበታል።
ጥናቱ የቀረበው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከ Welthungerhilfe (WHH) ጋር በመተባበር ባዘጋጀው የመማማሪያ እና የልምድ ልውውጥ መድረክ ነው።
የጥናቱ ዋና አላማ የሲቪል ማህበረሰብ ሴክተር እያጋጠመው የሚገኘውን የፈንድ እጥረት ለመቅረፍና ዘላቂ የገቢ ምንጭ አማራጮችን ለማመላከት እንዲሁም ከተረጅነት የተላቀቀ ዘርፍ እንዲሆን ያለመ ሲሆን በኢትዮጵያ የሶሻል ኢንተርፕራይዞችን የሚመራ የህግ ማእቀፍ የሌለ በመሆኑ ምክንያት አማራጩን ለመጠቀም ተግዳሮት የፈጠረ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲገለጽ በመቆየቱ እና ባለስልጣን መስሪያቤቱም የጀመረውን ሴክተሩን የማጠናከርና የመደገፍ ተግባር መሆኑን በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገልጸው።
በጥናቱ ዝርዝር ሪፖርትን ጨምሮ የ’ፖሊሲ ሪኮመንዴሽንና ‘ፖሊሲ ብሪፍ’ እንደሚዘጋጅ ይጠበቃል ብለዋል።


የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መ/ቤቱ ይህንን ጥናት ለማካሄድ የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀው ሴክተሩ እያጋጠመው ያለውን የፋይናንስ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ገልጸው እንደ Corporate Social Responsibility (CSR) ጨምሮ ሌሎች አማራጮች ላይም ትኩረት እንዲደረግ ጠይቀዋል። በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገለጹት CSR ን ጨምሮ ሌሎች ሴክተሩን የሚጠቅሙ ጥናቶችን ለማካሄድ ባለስልጣን መ/ቤቱ ቁርጠኛ መሆኑን ገልጸው ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የበጀት እጥረት ስላለ ይህንን ጉዳይ ለመደገፍ ፈቃደኛ አካላት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በመድረኩ ላይ በ EU CSF+ ፕሮጀክት የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች እና ልምዶች ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ በፕሮግራሙ ለታቀፉ 28 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር የፈንድ ድጋፍ የፊርማ ስነ-ስርአት ተከናውኗል።

