
ሎካላይዜሽንን አጀንዳ ያደረጉ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ህብረት (Consortium) መሰረቱ፡፡
ሎካላይዜሽንን አጀንዳ ያደረጉ ሃያ የሃገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ህብረት (Consortium) መሰረቱ፡: በምስረታው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም Consortium of Humanitarian Actors for National Growth and Empowerment (CHANGE ) መመስረቱ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ከአደጋ ምላሽ ሥራ ይልቅ የአደጋ ክስተቶች ላይ በማተኮር አይበገሬነትን እና የሰብኣዊ ድጋፍ ሉዓላዊነት ላይ ውጤታማ ሥራ ለመስራት ሁሉም የሚመለከታቸው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመተባበር በቅንጂትና በቁርጠኝነት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አክለውም ሎካላይዜሽንን ስናስብ ወደ ውስጥ መመልከት ፣ከተረጂነት መላቀቅ ቀድሞ ተዘጋጅቶ ለችግሮች ምላሽ መስጠት ላይ ትኩረት ማድረግ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ በዚህ ዙሪያ ከሲቨል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢፌደሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያቤቱ የምዝገባ ስርዓቱን በማዘመን፣የክትትልና ድጋፍ በማጠናከርና የቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓትን ከመገንባ አንጻር በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡:
የኢፌዲሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተመዘገቡበት ዓላማ መሰረት ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እንዲያደርጉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሎካላይዜሽን አጀንዳ በሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ ውሰጥ ካሉ ስትራቴጅክ ጉዳዮች መካከል አንዱ በመሆኑ የሎካላይዜሽን የስራ ቡድን (Localization Task Force) ከመመስረት ጀምሮ ይህም መድረክ እንዲሳካ ባለስልጣን መስሪያቤቱ የሙያና የቴክኒክ ድጋፍ አድርጓል ብለዋል፡፡
Consortium of Humanitarian Actors for National Growth and Empowerment (CHANGE) መመስረቱም የሃገር በቀል እና የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፍ ለሚሹ የማህበረሰብ ክፍሎች መርህ ላይ የተመሰረተ ድጋፍ እንዲያደርጉ አድል የሚሰጥ በመሆኑ ባለስልጣን መስሪያቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ያደርጋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ለሚገጥሙ ችግሮች ወቅታዊ እና የተቀናጀ የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሁሉም የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት በቅንጅና በትብብር መስራት ይኖርበታል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዶ/ር አንበሱ ቶላ የCHANGE Consortium የቦርድ ሰብሳቢ በመድረኩ ለተሳተፉ እና ፕሮግራሙ እንዲሳካ ትብብር ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ሃገር በቀል ድርጅቶች በጋራ በመሆን የመሰረትነው ድርጅት ለችግሮች ምላሽ ለመስጠት ብቻ ሳይሆን የረጅም ጊዜ የልማት እቅድ በመቅረጽ በሀገር ውስጥ ቅድሚያ በሚሰጣቸውን ጉዳዮች ላይ ትርጉም ባለው መልኩ አስተዋፅዖ ለማበርከት ነው ብለዋል፡፡
CHANGE Consortium በብሔራዊ ደረጃ የሰብአዊ እርዳታ ተዋናዮች መካከል ቅንጅታዊ የአሰራር ስርዓት መፍጠር፣ የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች መስጠት፣ፍትሃዊና ተደራሽ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲኖር ማስቻል ፣ሁሉም ፕሮግራሞች ለሴቶች፣ ህጻናት እና አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ያደረጉ መሆናቸውን ማረጋገጥ እና ሌሎች ዓላማዎችን ተፈጻሚ ለማድረግ የተቋቋመ ሃገር በቀል ድርጅት ነው፡፡


