በተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የተመራ ልዑካን ቡድን MSI ኢትዮጵያ በጅማና አከባቢው ያከናወናቸውን ስራዎችን ጎብኝተዋል፡፡

በጉብኝቱ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችን ጨምሮ የተከበሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በህዝብ ተወካዬች ምክርቤት የሰው ሃብት ልማት፣ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዬች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ፣አምባሳደር ፍጹም አረጋ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እና ሌሎች የክብር እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

MSI ኢትዮጵያ ከሱማሌ፣ጋንቤላና ቤኒሻጉል ውጭ በሁሉም ክልሎች በጤና ዘርፍ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ የውጭ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን በእናቶች የስነተዋልዶና ምክር እና አገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ በሃገራችን በተለያዩ ሶስት መቶ ጤና ተቋማት ላይ እንደሚሰራ የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ሽብሩ ገልጸዋል፡፡

በጅማ ዞን ማና ወረዳ ኬንተሪ ቀበሌ ኬንተሪ ጤና ኬላ እና የቡ ጤና ጣቢያ ላይ MSI ኢትዮጵያ በተንቀሳቃሽ የጤና ቡድን አማካይነት የተደራሽነት ችግር ያለባቸው አከባቢዎች ላይ በመሄድ የቤተሰብ እቅድን ጨምሮ ሌሎች የስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎቶችን፣የስርዓተ ምግብ ልየታ እና ወደ ጤና ተቋማት ሪፈር የማድረግ ስራ፣የእናቶች ጤና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ይሰራል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመንግስት ጤና ስርዓት ግንባታ ላይ በስልጠናና በክትትል የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት፣ መሰረታዊ የቁሳቁስ ድጋፍ በሟሟላት፣ የእውቀት ሽግግር በማድረግ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረው ማስቻል እና የልምድ ልውውጥን ጨምሮ የመማሪያ ፎረም ማዘጋጀት ስራዎችን መስራቱን በጉብኝት ወቅት ለመረዳት ተችሏል፡፡

Click the button

ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ በሰጡት አስተያየት MSI ኢትዮጵያ ተደራሽ ያልሆኑ አከባቢዎች ላይ በመሄድ ማኅበረሰቡን ለማገልገል እና የእናቶችን ህይወት ለመታደግ የሰራውን ስራ አመስግነው ድርጅቱ ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ ከዚህ ዘርፍ ውጭ ለመስራት ማሰብ ይኖርባችኃል ሲሉ ገልጸዋል፡:

አቶ ፋሲካው ሞላ የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተር በሰጡት አስተያየት ባለስልጣን መስሪያቤቱ አንዱ ተግባሩ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ሲሆን አሁን MSI ኢትዮጵያ የሰራቸውን ስራዎች መመልከት መቻሉ የሱ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሎካላይዜሽን ጉዳይ ትልቁ የባለስልጣን መስሪያቤቱ አጀንዳ መሆኑ በመግለጽ ድርጅቱ ከዚህ አንጻር መንግስት በፈቀደው የገቢ ማስገኛ (IGA) በመጠቀም ከጥገኝነት በመላቀቅ እራስን ለመቻል የተሰራው ስራ አበረታች ነው ብለዋል፡፡

MSI ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሞዴሉ በጣም ጥሩ እና ለሌሎችም ምሳሌ ነው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የሶሻል ኢንተርፕራይዝን በተመለከተ ከባለስልጣኑ እና ከሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ጥናት ቢሰራ ጥሩ ነው በማለት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዚህ ሂደት ልዩ ትኩረት የሚሹ የማህረሰብ ክፍሎች ሴቶችና ህጻናት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራው ስራ መበረታታት እንደሚገባው ገልጸው ድርጅቱ ሞዴል ፣ ለሌሎች ምሳሌ እና ማህበረሰቡን የሚጠቅም ተቋም እንዲሆን ከዚህ የበለጠ መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በማጠቃለያ ንግግራቸው እደገለጹት በነበረው ቆይታ እና ጉብኝት ምስጋናቸውን አቅርበው ሁሉም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን ሲሰሩ ሀገርን እና ማህበረሰቡን ታሳቢ አድርገው መሆን ይጠበቅበታ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የዚህ መድረክም ዓላማ የተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ በማድረግ ገንቢ ሃሳብ ለማግኘትና ቅንጅታዊ አሰራርን የበለጠ ለማጎልበት መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንም ከክትትልና ከቁጥጥር ባሻገር ድጋፋዊ እገዛ ስላደረገ የሰርትፍኬት ሽልማት MSI ኢትዮጵያ ተበርክቶለታል፡፡ ከጉብኝቱ በተጨማሪ ድርጅቱ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት እና ሎካላይዜሽንን በተመለከተ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Click the button