
በደቡብ ፈረንሳይ ሰላም ኢትዮጵያ መረዳጃ ማህበር ከወንድም ካሊድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በኢፌደሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ትብብር ለጎንደር ዩኒቨርስቲ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ለወልዲያ አጠቃይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እና ለኮንቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል 30 ሚሊየን ብር የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ፡፡
በርክክብ ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ፣የባለስልጣን መስሪያቤቱ ም/ዋና ዳይሬክተሮች አቶ ፋሲካው ሞላ እና አቶ መስፍን ሙሉነህ፣የፋውንዴሽኑ ም/የቦርድ ሰብሳቢ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ፣የሶስቱ ሆስፒታሎች ተወካይ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ክብርት ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር የበጎ ፍቃድ ስራ አስኪለመድ ግዜ ይወስዳል ነገር ግን ከተጀመረ በኋላ ባህል መሆን እንደሚችል ካሊድ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በኮቪድ ወቅት በራሳቸው ፍቃድ በራቸውን ከፍተው ማዕድ ያጋሩበትና ለሰው የደረሱበት ተግባር ዘር ሆኖ እዚህ ደርሷል በማለት አሁንም ግለሰብ፣ቤተሰብ እና ማህበረሰብ የሚገነባበት ቤት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት በፋውንዴሽኑ በርካታ ከጎዳና ላይ የሚኖሩ ወጣቶችና ሴቶችን ስልጠና በመስጠትና እራሳቸውን እንዲችሉ ማድረጉን እና በሃገራዊ ጉዳዬች ላይ የችግኝ ተከላ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታ፣የአቅመ ደካማ ቤቶች ግንባታ ስራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል፡:
አምራች ዜጋ እንዲፈጠር ህጻናት በመጠለያ እንዲያድጉ የተደረገውን ስራ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትልቅ ክብር አለው ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ ወንድም ካሊድ ፋውንዴሽንን የመሰሉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችን የመመዝገብ ብቻ ሳይሆን ድጋፍ የማድረግም ሃላፊነት ባለስልጣን መስሪያቤቱ ስላለበት ለሌሎችም ሞዴል እንዲሆን እንሰራለን ብለዋል፡፡
ፋውንዴሽኑ ከዚህ ቀደም በአጭር ጊዜ ጥሪ ሰብዓዊ ድጋፍ ላይ መሳተፋን ገልጸው የዛሬው ድጋፍም ከዚህ ቀደም በገቡት ቃል መሰረት የፈጸሙት መሆኑን በመግለጽ ለዚህ ሁሉ ድጋፍ መነሻ የሆኑትን በደቡብ ፈረንሳይ ሰላም ኢትዮጵያ መረዳጃ ማህበርን አመስግነዋል ፡፡
ወንድም ካሊድ በሰጠው ማብራሪያ አሁን ላይ በፋውንዴሽኑ 120 እናቶች ከነልጆቻቸው እና ከ400 በላይ ወጣቶች መኖራቸውን ገልጸው የዛሬው ድጋፋ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተፈጠረው ችግር ምክንያት ድጋፍ ለማድረግ የተሰራ ስራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ፋውንዴሽናቸው ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት የሚሰራ ሲሆን በልዩ ሁኔታ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እና ET ፋውንዴሽንን አመስግነዋል፡፡ በመጨረሻም ድርጅቱን የመጎብኘት እና ማዕድ የማጋራት ስራ ተሰርቷል፡፡


