
በሁለትዮሽ ስምምነት የሚሰሩ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደ ባለስልጣኑ ቀርበው ምዝገባ ካላከናወኑ እርምጃ እንደሚወስድ ተጠቆመ።
ይህ የተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ክፍለ አህጉራዊ፣ አህጉራዊ ወይም ዓለምአቀፋዊ ዓላማን ለመተግበር የሚቋቋሙ ድርጅቶችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ ላይ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅት ነው።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ክፍለ አህጉራዊ፣ አህጉራዊ ወይም ዓለምአቀፋዊ ዓላማን ለመተግበር የሚቋቋሙ ድርጅቶችን ለመመዝገብና ለማስተዳደር የሚያስችል ረቂቅ መመሪያ አዘጋጅቶ ከሚመለከታቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርጓል።
የውይይት መድረኩን በንግግር ያስጀመሩት የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ አህጉራዊና ክፍለአህጉራዊ ዓላማን ለማስፈፀም ተቋቁመው በሁለትዮሽ ስምምነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በባለስጣኑ መመዝገብ ያለባቸው መሆኑን ጠቁመው ይህንም ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የተለየ አሰራር መዘርጋቱን ጠቁመዋል።
በሁለትዮሽ ስምምነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደባለስልጣኑ ቀርበው የማይመዘገቡ ከሆነ ህግን እንደተላለፉ ተቆጥሮ ህግን ለማስከበር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ የጠቆሙ ሲሆን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ህግን አክብረው ለሚመዘገቡ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ በመግለጽ በባለስልጣኑ ቀርበው ያልተመዘገቡ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንዲመዘገቡ ጥሪ አስተላልፈዋል።

