የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ሀገራዊ የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባትን የሚያረጋግጥ ተግባራትን በጋራ ለማከናወን የትብብር ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሰላም ግንባታ ስራዎች ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና አላቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በተለይም ከሪፎርም በኋላ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጁ መሻሻልና ሌሌች ተያያዥ ተግባራት በዘርፉ ለውጥ እንዲመጣ የመንግስትን ቁርጠኝነት ያመላክታል ብለዋል፡፡
ክቡር ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) ይህ ስምምነት የሰላም ስራ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በፍቃደኝነት የሚሰሩ ተቋማት፣ ቡድኖችና ግለሰቦችን ለማበረታታትና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በሰላም ግንባታ ሂደት ላይ የድርሻቸውን እንዲወጡ የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
ከባለስልጣኑ ጋር በቅንጅት መስራት ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ከይረዲን ለስኬቱ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው በተቋማችን የሰላም እሴት ግንባታ ላይና የግጭት አፈታት ስራዎችን ለመስራት የተመዘገቡ 349 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች መኖራቸው ጠቅሰው የሲቪል ማህበረሰቡን በማቀናጀት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የድርሻቸውን ለመወጣት የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡ ሰምምነቱ በሁለቱ ተቋማት መካከል ዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደሚያግዝም የተገለፀ ሲሆን በቀጣይ የጋራ ተግባራትን ለመምራት የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ ለማቋቋምም ተስማምተዋል።
Click the button