የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰብዓዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ባለፈ የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠርና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት እንዲኖር የሚያስችል አገልግሎት መሆኑን የባለሰስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ጠቆሙ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከባህር ተሻጋሪ የበጎ ፈቃደኞች ድርጅት (Voluntary Service overseas VSO) ጋር በመተባበር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ካንፓሶች ለተውጣጡ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ትኩረት ያደረገ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናው የዩኒቨርሲቲውን ተማሪዎች አቅም በማጎልበት በዩንቨርሲቲው የሚገኙ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ክበባትን ለማጠናከርና በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህልን ለማሳደግ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡
ስልጠናውን ያስጀመሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና በጎ አድራጎት ተግባራት ያለምንም ልዩነት የሰብዓዊነት መርህን ብቻ መሰረት ባደረገ መልኩ የሚከወን ተግባር መሆኑን ጠቁመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከሰብዓዊና ማህበራዊ ጠቀሜታው ባለፈ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በመቅረፍ የተረጋጋ ማህበረሰብን ለመፍጠርና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትና እድገት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት በዋነኛነት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በስፋት እንዲሳተፉና በጎ ፍቃደኛ ትውልድን ማበረታታት ይቻል ዘንድ በሀገር ውስጥ ለሚገኙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን መስጠት እና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ክበባትን ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡




ባህር ተሻጋሪ በጎ ፈቃደኞች ወይም በእንግሊዘኛው አጠራር Voluntary service overseas (VSO) የኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ተመስገን ዓለሙ በበኩላቸው ድርጅታቸው Voluntary service overseas VSO ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት እንዲስፋፋ በመስራታቸው መደሰታቸውን ገልጸው ስልጠናው በጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነትን በሚመለከት ጠቃሚ ግንዛቤ የሚጨብጡበት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው ጋር አብረው የበጎ ፈቃድና የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በጊዜ እንዲያስቡትና በበጎ ፍቃድ ተግባራት ላይ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ በር የሚከፍት መሆኑን አንስተው ተማሪዎች ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ከባለሰልጣን መስሪያ ቤቱ እና ከ VSO ጋር በጋራ በመሆን የግንዛቤ ማስስበጫ ስልጠናዎችን ለዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የሚሰጡበት ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
በስልጠናው ማጠቃለያ ላይ ተገኝኝው የማጠቃለያ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው በጎ ፈቃድ አብሮነትን፣ እርስ በርስ መደጋገፍን፣ አንድነትንና መተሳሰብን የሚያመጣ በመሆኑ በጎ ፈቃደኛ ትውልድ መገንባት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው እንደሀገር ያሉ ስብራቶችን ለመጠገን በጎ ፈቃድ አገልግሎት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነት ጉዳይ ሀገርን የመገንባት ትልቅ ጉዳይ መሆኑን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት በተለይም በትምህርት ላይ ለሚገኙ ወጣቶችና ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ቢሰጥ በጎ ፍቃድን ባህሉ ያደረገ ትውልድን የሚፈጥርና ሀገርን የሚገነባ እንደሆነ አንስተው በተለይ በዩኒቨርሲቲዎችና በወጣቶች ላይ መስራት የበለጠ ውጤት እንደሚያመጣ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ትውልድን የመገንባት ስራ ስለሆነ ለሌሎች ግንዛቤውን ከመፍጠር ባሻገር በበጎ ፍቃድ ተግባራት ለይ መሰማራት ተገቢ እንደሆነ የጠቆሙ ሲሆን በዚህ ረገድ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና የዩኒቨርሲቲው አመራርም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዩኒቨርሲቲው የሚሰራው ስራ ስኬታማ መሆን በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረገውን ጥረት ውጤታማ ለመሆኑ ማሳያ ሊሆን የሚችል በመሆኑ አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግም አክለው ገልጸዋል፡፡
ስልጠናውን ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን፣ ከVoluntary Service Overseas VSO አቶ ጌታያውቃል አብርሃም እንዲሁም ከሊቭ ፎር ጀነሬሽን ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ብርሃኑ የሰጡ ሲሆን Essence of voluntarism, Social Accountability, Social Inclusion and Gender in Volunteerism, VSO and Volunteerism፣ Facilitations Skill በሚሉ ርዕሶች ላይ ንድፈ ሀሳብንና ተግባርን ባካተተ መልኩ ተማሪዎች ስልጠናውን እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡





