የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በተለያዩ ፕሮግራሞች አክብሯል፡፡

በፕሮግራሙ በዲሞክራሲ ማስተባበሪያ ማዕከል የሲቪል ባህል ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ደስታ ብዙአየሁን ጨምሮ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ፣ም/ዋና ዳይሬክተር ፣የተቋሙ ሰራተኞችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንዳሉት በሃገር አቀፍ ደረጃ የዘንድሮው የሴቶች ቀን አከባበር ከወትሮው በተለየ መልኩ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሴቶች ላይ በተጨባጭ የተሰሩ ስራዎችን ምልከታ በማድረግ፣በአካል ከማህበረሰቡ ጋር በመገኘት እና የሀገራችን ሴቶችን ፍላጎቶችና አንገብጋቢ ችግሮች ከራሳቸው አንደበት በማዳመጥ የተካሄደ እንደነበር ገልጸው የዚህን አመት አለም አቀፍ የሴቶች ቀን የተገኙ መልካም ተሞክሮዎች በመቀመር ወደ ሌሎች አካባቢ እንዲስፋፉ ለማድረግ እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት የራሳቸውን ድርሻ በመውሰድ ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ በማብቃት ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው አቅጣጫ መቀመጡን አንስተዋል፡፡
ከዚህ ረገድ በባለስልጣን መስሪያቤቱ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዓላማቸውን ለማሳካት ሲንቀሳቀሱ የሴቶችና የህጻናትን እንዲሁም ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን አካተው እንዲሰሩ ማድረግ እና ቀኑን ከማክበር በዘለለ በባለስልጣን መስሪያቤቱ ያሉ ሴት ሰራተኞችን አቅም በማጎልበት ፣ ውጤታማ ሴቶች ወደ ፊት በማምጣት፤የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በመቅረፍ እና የስርዓት ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ውስጥ የወንዶችም ሚና እንዲጎብት በማበረታታት ረገድ በትኩረት መስራት ይጠይቃል ብለዋል፡፡
የተቋሙ ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳዬች አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ትግስት አቡዬ በበኩላቸው የዘንድሮው አለም አቀፍ የሴቶች ቀን /ማርች 8/ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ114ኛ ጊዜ “For ALL Women and Girls: Rights. Equality. Empowerment.” በሚል መሪ ቃል እና በሃገራችን ደግሞ ለ49ኛ ጊዜ “ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ሁሉን አቀፍ ለውጥ በሴቶች ተሳትፎ ይረጋገጣል’’ በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ገልጸው የሴቶችን ሁንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሁሉም ረገድ መከናወን የሚገባቸው ተግባራትን በመለየት ትኩረት ተሰጥቶት ይሰራል ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ ወ/ሮ ማርያ ሙኒር የሴቶች ማረፍያ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ የህይወት ተሞክሯቸውን ለሰራተኞች ያካፈሉ ሲሆን በንግግራቸውም በምንም ሁኔታ ውስጥ ሴቶች ተስፋ መቁረጥ እንደሌለባቸውና አልችልም የሚል መንፈስ ሊኖራቸው እንደማይገባ አንስተዋል፡፡
ሌላው በእናት ባንክ ለሰራተኞች የቁጠባ ባህልን እንዲያጎለብቱ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡