
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ያላቸውን የስራ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ለማድረግ የሚያስችል የውይይት መድረክ ተካሄደ።
ውይይቱ የካቲት 22 ቀን 2017 በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮችና አና ስራ አስፈጻሚ አባላት እንዲሁም ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት የስራ አስፈጻሚ አባላትና ሴክሬታሪያት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በጋራ በሚሰሩ ጉዳዬች ላይ የመከሩ ሲሆን በዚህ መድረክም በሁለቱም አካላት በተውጣጡ ኮሚቴዎች አማካኝነት የተዘጋጀ ረቂቅ ስትራቴጂያዊ የትብብር ማዕቀፍ ሰነድ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ግብዓት የማሰባሰብ ስራ ተሰርቷል፡፡ ባለስልጣኑ በአዋጅ በተሰጠው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የመመዝገብ፣ የመቆጣጠርና ድጋፍ የማድረግ ተልዕኮው መሰረት በማድረግ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም ዘርፉን የሚወክል ተቋም ከመሆኑ አንጻር ከምስረታው ጀምሮ አገራዊና ዘርፉን የተመለከቱ ጉዳዬችን በትብብር እና አጋርነት ሲሰራ ቆይቷል፡፡
ሁለቱ ተቋማት ትብብሩን ስትራቴጂያዊ ማድረግ ወጥነት ባለው መልኩና በዘላቂነት ለማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑ ስለታመነበት የትብብር ማዕቀፉ ሊዘጋጅ እንደቻለ በመድረኩ ተገልጿል።
ማዕቀፉ ተቋማቱ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያረጋገጠና በአገራዊ ጉዳዮች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርግ ጠንካራ የሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ ለመገንባት ያላቸውን የጋራ አላማ ውጤታማ በማድረግ ረገድ አጋዥ እንደሆነ በመግለጽ በመድረኩ የተሰጡ ግብአቶች ተካተው በአጭር ጊዜ እንዲቀርብና በተቋማቱ በጋራ ጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ አቅጣጫ ተሰጥቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ በተከሰቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ፣የእግድ ላይ በሚገኙ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና የUSAID ጊዜያዊ የሥራ ማቆም ውሳኔ በሴክተሩ ላይ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ በተመለከተ ሰፊ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የመፍትሄ ሃሳቦች ተነስተው አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ ተጠናቋል፡፡

