
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ትምህርት ለልማት ከተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር የሶስት ሚሊየን ብር የፈንድ ድጋፍ ስምምነት አድርጓል፡፡ ባለስልጣኑ የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶችን የመደገፍና የክትትል ስራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትምህርትን ማዕከል በማድረግ የተለያዩ የልማትና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፎች ላይ ትኩረት አድርጎ ለሚሰራው ትምህርት ለልማት ለተባለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የፈንድ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የስምምነት ሰነዱን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት የድርጅቱ የፕሮግራም ኃላፊ አቶ ቶቾ ኢንኮሶ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያገኙትን ድጋፍ በምስራቅ ወለጋ ዞን ሳሲጋ ወረዳ በሎ ቀበሌ ላይ በመጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃይ ዜጎች እንደሚያውሉት በመግለጽ በአጭር ጊዜ ለማድረስ በአካባቢው ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ ቀደም ሲል በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ከተመሰረተበት 1991 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርት፣ በጤና፣ እና በልማት ስራዎች ላይ እንዲሁም በሰላም ግንባታ ላይ ለረጅም ጊዜ ሲሰራ መቆየቱን አንስተው በአካባቢው በተለያዩ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ የማህበረሰብ ክፈሎች የአስቸኳይ የምግብ እህል ድጋፍ ለማድረግ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር ስምምነት ላይ እንደደረሱ ጠቁመዋል፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አስተዳደርና ንብረት ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ መስቀሉ መንበሩ እንደገለጹት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በመደገፍና ከፈንዱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል፡፡
አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ፈንድ አቅም ውስን ቢሆንም ያለውን ውስን ሃብት በአግባቡ በመጠቀም የማህበረሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው በቀጣይም ፈንዱ የሚጠናከርበትን መንገድ በመቀየስ በርካታ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

