አስቸኳይ መግለጫ
ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ
የኢትዮጵያ መንግስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከየትኛውም ህጋዊ ምንጭ ሃብት በማሰባሰብ በህጋዊና ሞራላዊ በሆኑ ዓላማዎች ላይ መስራት እንደሚችሉ የሚደነግግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 አውጥቶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ምንጭ የሚያገኙትን ሃብት በህግ መሰረት በመጠቀም በስራቸው የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚገባቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ይህንንም ለማሳካት ባለስልጣን መ/ቤታችን አስፈላጊውን የክትትልና ቁጥጥር ስራዎችን እያከናዎነ ይገኛል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ባለስልጣን መ/ቤቱ በየጊዜው በዘርፉ የሚከሰቱ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በቅርበት በመከታተልና አንድምታቸውንና ተፅዕኖዎቻቸውን በመተንተን አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሁም ክትትል ያደርጋል፡፡
ከሰሞኑ በአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (ዩ.ኤስ.ኤይድ) በኩል የእርዳታ ማቆም ውሳኔ የተወሰነ መሆኑን መረዳት ተችሏል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤታችን ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ሲሆን ዝርዝር ሁኔታዎችን መሰረት በማድረግ በቀጣይ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል የሚያከናዎን ይሆናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆነ በአሁኑ ወቅት ከዩ.ኤስ.ኤይድ የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙ ድርጅቶች ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ያለ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ግልፅ ፍቃድ ንብረት የማስተላለፍ፣ የማስወገድ ወይም የመሸጥ ወይም ከመደበኛ/ፕሮጀክት ስራዎች ጋር ተያያዥ ከሆኑ ጉዳዮች ውጭ በማናቸውም መልኩ ሃብትና ገንዘብን ለሶስተኛ ወገን ማስተላለፍ የተከለከለ መሆኑን በጥብቅ እናሳስባለን፡፡ ይህንን ማሳሰቢያ በመተላለፍ በሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ላይ ባለሥልጣን መ/ቤቱ ተገቢውን እርምጃ የሚወስድ መሆኑን እናሳውቃለን፡፡
ጥር 27 ቀን 2017
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ