የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ለሚገኙ ሴት ታራሚዎች አገልግሎት የሚውል ድጋፍ አደረገ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለትምህርት፣ ለሴቶች ንጽና መጠበቂያ እና ለህጻናት አልሚ ምግብ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቁሳቁሶችን የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የማረም ማነጽና ተሃድሶ ልማት ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ጄኔራል ሉባባ ጀማል በተገኙበት በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ድጋፍ አድርጓል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለሴቶችና ህጻናት አገልግሎት የሚውሉ የትምህርት ቁሳቁሶችን አሜን ከተባለ ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት የተረካባቸው ሲሆን ድጋፎቹም በዋናነት ሴቶችና ህጻናትን ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ለማገዝ የተደረገ ነው፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የትምሀርት ቁሳቁሶቹን ከድርጅቱ በተቀበሉበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ቀደም ሲል በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ጉብኝት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ባደረጉት ጉብኝት የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በመገንዘባቸው ከድርጅቱ የሚገኘው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ለማዕከሉ እንደሚሰጥ ድጋፉን ከአሜን የበጎ አድራጎት ድርጅት በተቀበሉበት ወቅት ጠቁመው ነበር፡፡
ይህንኑ ተከትሎ የተቋሙ የስራ አመራር አባላት በማዕከሉ በመገኘት የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የማረም ማነጽና ተሃድሶ ልማት ዘርፍ ም/ኮሚሽነር ጄኔራል ሉባባ ጀማል በተገኙበት ድጋፍ አስረክበዋል፡፡
ድጋፉን የተረከቡት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ሉባባ ጀማል ባደረጉት ንግግር በእርምት ላይ የሚገኙ ሴቶችና ህጻናትን በመደገፍ ረገድ ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው መሆኑን ጠቁመው በተለይ በማዕከሉ ለሚደረገው የመማር ማስተማር ሂደት ወቅቱን የጠበቀ ድጋፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ያለወንጀላቸው በማዕከሉ ለሚገኙ ህጻናትም የአልሚ ምግብ ድጋፍ መደረጉ ትልቅ አስተዋጽዖ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ አካቶ ትግበራ ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጸሀይ ሽፈራው በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በማስተባበር ለተለያዩ ማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ ሴቶችና ህጻናት ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸው በማዕከሉ ለሚገኙ ሴቶችና ህጻናት በመጠኑም ቢሆን ወቅታዊ ችግራቸውን ለመቅረፍ በሚል የተደረገ ድጋፍ መሆኑን አንስተዋል፡፡ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያደረገው ድጋፍ የመጀመሪያ መሆኑን ጠቁመው ለማዕከሉ አገልግሎት የሚውሉ መሰል ድጋፎችን ማድረጉን እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
የሴቶች ማረሚያና ማረፊያ ማዕከል ዳይሬክተር ኮማንደር አይናለም ሳህሉ የሲቪክ ማህረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ያደረገው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ድጋፍ በእርምት ሂደት ላይ ለሚገኙ ሴት የህግ ታራሚዎች በቆይታቸው የግል ንጽናቸውን እንዲጠብቁ የሚያስችል መሆኑን ገልጸው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፡፡