
የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በጋምቤላ ክልል በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር ከሶስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነቡትን የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች አስረክበዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ አለሚቱ ኡሞድ እንዳሉት ከለውጡ በኃላ በክልሉ በርካታ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸው፣ በተለይም ሰው ተኮር የሆኑ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎች ማህበረሰቡን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆኑን አውስተዋል፡፡
የበጎ ፍቃድ ስራዎች አንድነትን የሚፈጥሩ በመሆኑ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሯ ፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት በክልሉ በበጎ ፍቃድ ስራ ላይ ተሰማርተው ግንባታውን አጠናቀው ለአቅመ ደካሞች በማስረከባቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የተከበሩ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው ማህበራዊ ሰው ተኮር ልማቶች በሀገራችን መጎልበት አለባቸው ያሉ ሲሆን፣ በተለይም ወጣቶችን ለበጎ ፍቃድ አገልግሎት በማስተባበር በማህበረሰቡ ውስጥ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ማገዝ እንደሚገባ በማሳሰብ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የማህበረሰቡ ባህል መሆን እንደሚገባው አመላክተዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት ከመደበኛ ስራ በተጨማሪ በማህበራዊ ሃላፊነት ዙሪያ ባለፉት ዓመታት የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማትን በማስተባበር በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራዎችን ማከናወን መቻሉን አስታውሰው፣ በጋምቤላ ክልልም ለአምስት አቅመ ደካሞች የቤት ግንባታ በማከናወን በዛሬው ዕለት ርክክብ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ 1113/2011 መሰረት የበጎ ፍቃድ ስራን በማህበረሰቡ ዘንድ ባህል ለማድረግ በተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት መሰረት በርካታ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡


