
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮንሶ ዞን ጃርሶ ቀበሌ የማኅበረሰቡን ችግር የቀረፈ ፕሮጀክት፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ብ/ክልላዊ መንግስት ኮንሶ ዞን በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ የተሰሩ ፕሮጀክቶች በዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በተመራ ልዑካን ቡድን ተጎብኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ ኢየሱስ በኮንሶ ዞን ጃርሶ ቀበሌ ያንዳ ፋሮ ሰገን ሰዋቴ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት በአከባቢው ያሉ አንድ ሺህ አባወራን በመስኖ እና አምስት መቶ አባወራ ከብት በማደለብ ተጠቃሚ ማድረጉን የፕሮጀክቱ ፕሮግራም ኦፍሰርና ኢንጅነር አቶ ግዛቸው ቶሪያቶ አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ ኢየሱስ በአከባቢው በ1962 ዓ.ም በተከሰተ ድርቅ የእርዳታ ስራ መጀመሩን ገልጸው የእርዳታ እህል መስጠት ብቻውን ዘላቂ ለውጥ እደማያመጣ በማመን የፖሊሲ ለውጥ መደረጉን አብራርተዋል፡፡ በዚህም ለሰዎች እርዳታ በየጊዜው ከመስጠት ይልቅ አምርተው እራሳቸውን የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት እንደሚቻል በማሰብ በአከባቢው የሚገኘውን ወንዝ ወደ መስኖ ስራ መቀየራቸውን አብራረተዋል፡፡
በዚህ ስራ ድርጅቱ ከ PADD ከሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ 5850 ሄክታር መሬት የማልማት ስራ የሰራ ሲሆን ማህበረሰቡ ይህንን ተከትሎ ካናሎችን እና የመስኖ ስራዎችን በእጥፍ የማስፋፋት ስራ መስራታቸውን ገልጸው ፐሮጀክቱ ማህበረሰቡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረጉም ባሻገር ከባቢያዊ ሁኔታውን የቀየረ እና የአከባቢውን ነዋሪ የማህበራዊ መስተጋብርን በእጅጉ ያስተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት እንደ አቶ ጸጋዬ ያሉ ነዋሪዎችን ደግሞ ከእለት የእርዳታ ፍላጎት ወደ ባለሃብትነት መቀየር መቻሉን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
.
አቶ ጸጋዬ በኮንሶ ጃርሶ ነዋሪ ሲሆኑ በድርቁ ጊዜ በመካነ ኢየሱስ ቤተክርስቲያን እርዳታ ተጠቃሚ እና በኋላም በያንዳ ፋሮ ሰገን ሰዋቴ የምግብ ዋስትና ፕሮጀክት ስልጠና በመውሰድና በመስኖ ስራ ላይ በመሰማራት በወር በሙዝ ሽያጭ እስከ ሰላሳ ሺህ ብር ገቢ የሚያገኙ ባለሃብት መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ቀደም በአከባቢው ባለ ውሃ እንዴት መጠቀም እንዳለብን ባለማወቅ ብዙ ፈተናዎች ደርሶብናል ያሉት ሌላው የአከባቢ ነዋሪ መካነ እየሱስ ከመጣ በኋላ በመስኖ የሰብል እና የሙዝ ምርት በመጀመር ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው ድርጅቱ የሰራው ስራ ነዋሪውን ከሞት ወደ ህይወት የቀየረ እና ከስደት ያዳነ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስትያን መካነ ኢየሱስ በአከባቢው አስራ ሁለት ወተር ፖይንት መስራቱን እና ሶላር በመግጠም ፣በተለያየ ዘርፍ ስልጠና እና መነሻ ገንዘብ በመስጠት ማህበረሰቡ ከእርሻ በተጨማሪ ከብት በማደለብና የዶሮ እርባታ ላይ ተሰማርተው በኢኮኖሚ እንዲለወጡ ማድረጉንም አክለው አብራርተዋል፡፡ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ በኢትዮጵያ ለረጅም አመታት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው በጉብኝቱም በመሬት የሚታይና በተግባር የማህበረሰቡን ህይወት የለወጠ ፕሮጀክት በመመልከታቸው መደሰታቸውን ገለጸዋል፡፡
አያይዘውም ድርጅቱ የማህበረሰቡን ዘላቂ ተጠቃሚነት እና ከእርዳታ ይልቅ ሰርቶ መለወጥ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ያለውን ተግባር አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመግለጽ ተቋማቸውን በሚችለው ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ፕሮጀክት በገንዘብ የደገፈው PADD ሲሆን በዋናነት በፓርትነር በኩል የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡


