አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አገልግሎት መስጠት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ጉዳይ መሆኑን ተጠቆመ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አካል ጉዳተኞችን ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ተናገሩ፡፡ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዓለም ዓቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን፣ ዓለም ዓቀፍ የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀን፣ ዓለም ዓቀፍ የህጻናት ቀንንና ዓለም አቀፉ የጸረ ኤድስ ቀን የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች በተገኙበት ተከብሯል፡፡
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችን ኢትዮጵያ ፈርማ ስትቀበል ሁላችንም በተሟላ ሁኔታ ተግባራዊ እንድናደርገው መሆኑን ጠቁመው በተለይም አካል ጉዳተኞች ወደተቋሙ ለአገልግሎት ሲመጡ አስፈላጊውን ድጋፍና አገልግሎት መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
ተቋማችን ከሚወጣው ሃላፊነት በተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በዚህ ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር አካል ጉዳተኞችን የሚመለከቱ እና የጸረ ጾታዊ ጥቃት ቀንን የሚመለከቱ ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
Click the button


