እንኳን ለዓለም አቀፍ የበጎ ፍቃደኞች ቀን አደረሳችሁ!!
የዓለም በጎ ፈቃደኝነት ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት በመላው ዓለም ባሉ አብዛኛው ህብረተሰብ ውስጥ በጎ ፈቃደኞች ለኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያደርጋሉ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በፈቃደኝነት በልዩ ልዩ ተግባራት በመሳተፍ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች (MDGs) ለማሟላት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ከማበርከታቸውም ባሻገር ለወገኖቻቸው በእውቀታቸውና በጉልበታቸው እያገለገሉ የመንፈስ እርካታን በሰፊው እየሸመቱ ይገኛሉ፡፡
እንደ ዊኪፔዲያ ና ኢንሳይክሎፔዲያ መረጃ መሰረት በጎ ፈቃደኝነት ማለት በግለሰብ ወይም በቡድን ግለሰብን፤ቡድንን ወይም ድርጅትን ለማጎልበት ያለምንም ዓይነት የገንዘብ ድጎማ አገልግሎቶችን የምንሰጥበት ሒደት ነው:: በጎ ፈቃደኝነት ለበጎ ፈቃደኛው እና ወይም ለማህበረሰቡ በርካታ ጥቅሞች ሊኖሩት ይችላል:: በጎ ፈቃደኛነት የክህሎትን ልህቀት ከማጎልበቱም ባሻገር ብዙውን ጊዜ በጎነትን ለማራመድ ወይም የሰዎችን የሰብአዊ ሕይወት ለማሻሻል ይጥራል ፡፡ ብዙ በጎ ፈቃደኞች በሰለጠኑበት ወይም በተካኑት ሙያ እንደ ህክምና, ትምህርት, ወይም ድንገተኛ እዳታን የመሳሰሉ ዘርፎች የሚያገለግሉ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት እንደ አስፈላጊነቱ ግልጋሎት ይሰጣሉ፡፡
ተቋማችንም በአዋጅ 113/2011 ከተሰጡት ተግባራት መካከል በኅብረተሰቡ ዘንድ የበጎ አድራጎት እና በጎ ፈቃደኝነት ባሕል እንዲዳብር ማድረግ ሲሆን ይህንን በተመለከተ የበጎ ፈቃደኝነት ስራ ባህል እንዲሆን፣ በዩኒቨርስቲዎች፣በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣በማህበረሰቡ እና በተቋም ደረጃ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች፣የበጎ ፈቃደኝነት ማበረታቻና ስራ አመራር መምሪያ (Voluntarism promotion and management guidance note) ማዘጋጀት፤በጎ ፍቃድ አገልግሎ የሚሰጡ አካላትና በጎ ፍቃደኛን የሚፈልጉ ተቋማትን ማገናኘት የሚችል ሲስተም ተግባራዊ የማድረግ ስራ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡


