
ጠንካራ፣ በሃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ፣ አስተውሎት ያለው፣ እምነት የሚጣልበት እና በህዝብ ተቀባይነት ያለው የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ለመገንባት በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ።
ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ
ይህ የተባለው የሲቪል ማኀበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች ዙሪያ ስልጠና በተሰጠበት ወቅት ነው፡፡ በስልጠናው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ባስተላለፉት መልዕክት ባለፉት የለውጥ ዓመታት መንግስት ባካሄደው ሪፎረም የሲቪክ ምህዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲሰፋ መደረጉን ገልጸው የተጀመረው የሲቪል ማህበራት ሪፎርም የበለጠ እንዲጎለብት እና ሕብረተሰቡን በተጨባጭ እንዲጠቅም ቀጣይነቱን እና ውጤታማነቱን የሚያረጋግጡ ስራዎችን ለይቶ ማከናወን አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።
ከዚህ አኳያ በሰብዓዊ መብት መከበርና መስፋፋት ላይ ለመስራት የተቋቋሙ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት ትርጉም ባለው መንገድ እንዲወጡ ማስቻል በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ ጉዳይ ተደርጎ የተወሰደ መሆኑን አንስተዋል፡፡ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ እንደተደነገገው የሲቪል ማህበራት በተሰማሩባቸው መስኮች የአድቮኬሲ ስራዎችን የማከናዎን እንዲሁም ከየትኛውም ህጋዊ ምንጭ ሃብት በማሰባሰብ በልማት፣ በዴሞክራሲ እና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያለገደብ መስራት የሚችሉበት አውድ የተፈጠረ መሆኑ አንስተው ከአገራዊ ለውጡ በፊት ከነበረበት በእጣት ከሚቆጠሩ ጥቂት ድርጅቶች በአሁኑ ጊዜ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ለመስራት የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ቁጥር መጨመሩን ገልጸዋል።
የቁጥሩ መጨመር በአንድ በኩል የምህዳሩን መስፋት የሚያረጋግጥ ቢሆንም እነዚህ ድርጅቶች ህዝብንና አገርን የሚጠቅሙ ስራዎችን ማከናዎን ላይ በትኩረት ሊሰሩ የሚገባ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ሪፎርም ሲካሄድ እምነት የተያዘበት ጉዳይ በተሰማራበት መስክ መስራትን ከመብት ባሻገር እንደ አንድ ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት ወስዶ የሚንቀሳቀስ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ እንዲገነባ ማስቻል መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዚህ መንገድ ገንቢ የሆነ የትብብር መርህን (Constructive Engagement) በመከተል ችግሮችን በመሰረታዊነት መፍታት ላይ ትኩረት ያደረገ ተግባርን በሃላፊነት ስሜት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው እነዚህ ድርጅቶች የበለጠ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ የአገርን ፍላጎት (demand driven) መነሻ ባደረገ መልኩ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ መተግበር እና በትግበራ ሂደትም ህግ፣ መርህ እና የአገርና ህዝብ ተጠቃሚነት ማእከል ማድረግ ይኖርባቸዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፍዋል፡፡ በመጨረሻ መልዕክታቸውም ጠንካራ፣ በሃላፊነት ስሜት የሚንቀሳቀስ፣ አስተውሎት ያለው፣ እምነት የሚጣልበት እና በህዝብ ተቀባይነት ያለው የሲቪል ማህበራት ዘርፍ ለመገንባት በጋራ መንቀሳቀስ የሚያስፈልግ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ደግሞ አቅምን መገንባትና በዴሞክራሲ መርሆዎች የሚመራ የሲቪል ማህበራትን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ስልጠናው ትኩረት ያደረገው Human right based approach ፣የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችና የህግና ተርጓሚው የግንኙነት አግባብና ዙሪያ የሲማድ ራስን በራስ የማስተዳደር ሃላፊነትን ትኩረት ያደረገ ነው። ስልጠናውን ተቋማችን ከጀስቲስ ፎር ኦል እና የኢትዬጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት ጋር በጋራ በመሆን የተዘጋጀ ነው፡፡ የሲቪል ማህበራት ከየትኛውም ህጋዊ ምንጭ ሃብት በማሰባሰብ በማንኛውም ህጋዊ ዓላማ እንዲንቀሳቀሱ የተፈጠረላቸውን ነፃነት በኃላፊነት ስሜት መጠቀም ላይ ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባ መሆኑን ገልጸው በተለይም በሰብዓዊ መብቶች መከበር ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማህበራት በዘርፉ ሃላፊነት ካለባቸው የመንግስት ተቋማት ጋር በመተባበርና በመቀናጀት በአገራችን የዴሞክራሲ ባህል እንዲገነባ እና ስልጡን ማህበረሰብ እንዲፈጠር እሩቅ አስበው መስራት ይኖርባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

