4ተኛውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ዝግጅቶችን አስመልክቶ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ።

በመግለጫው የተቋሙ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፍሲካው ሞላ የኢፌዴሪ መንግስት ባለፉት የሪፎርም ዓመታት ካካሄዳቸውና ውጤት ካስመዘገቡ የሪፎርም እርምጃዎች መካከል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ያካሄደው ዘርፈ ብዙ ሪፎርም መሆኑን ገልጸው በዚህም የሲቪል ማህበራት የሃገረ-መንግስት ግንባታ ቁልፍ ተዋናይ መሆናቸው ላይ ግልጽ የፖሊሲ አስተሳሰብ በመያዝ የህግ ማሻሻል እና የተቋማት ሪፎርም በጥልቀት የተካሄዱ ሲሆን ዘርፉን የበለጠ በማጠናከር የህዝብ ጥቅምን የሚያረጋግጥ ሥራዎችን እንዲያከናውን የክትትልና የድጋፍ ሥራዎችን ላለፉት ተከታታይ የሪፎርም ዓመታት ተከናውኗል ሲሉ ገልጸዋል።
ይህንን ሪፎርም የበለጠ ለማጠናከር በየዓመቱ የሲቪል ማህበራት ሳምንት በተለያዩ ፕሮግራሞች እንደሚካሄድ ጠቅሰው በያዝነው ዓመትም ተቋማችን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር አራተኛው የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት (4th CSO Week) ከህዳር 27-29/2017 ዓ. ም በግዮን ሆቴል እንደሚያካሂድ አብራርተዋል።
ፕሮግራሙ ሲቪል ማህበራት በኢኮኖሚና ማህበራዊ አገልግሎቶች ረገድ በሃገራችን ውስጥ ያላቸውን አስተዋጽኦ ለማህበረሰቡ ለማስተዋወቅ እና መንግስት የግሉ ሴክተር ከሲቪል ማህበራት ጋር ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ ፕሮግራም መሆኑም ተገልጿል፡፡ የመክፈቻ ዝግጅት (Grand opening) ላይ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣አምባሳደሮች፤የግል የልማት አጋሮች እና ሶስት መቶ በላይ የሚሆኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዳይሬክተሮች በተገኙበት በደማቅ ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን ተገልጿል።