የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በብራንድ ኮሙኒኬሽን፣ በህትመትና ኤሌክትሮኒክስ ፕሮዳክሽኖች፣ በሁነትና ተያያዥ ሥራዎች እንዲሁም በልዩ ልዩ የተግባቦት ሥራዎች ላይ በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ በኢትዮጵ ዜና አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ተፈራርመዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እና የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤተልሄም አበባው የተፈራረሙ ሲሆን የስምምነት ሰነዱ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ለማስፈጸም የሚያስችሉ የህዝብ ግንኙነት ስራዎችን ለመተግበርና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ለመወጣት እንዲሁም ተቋማዊ አሰራሩን ለማዘመን የሚያስችሉ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ስራዎችን በመስራት ለባለድርሻ አካላት ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል ዓላማን ያነገበ ነው፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዘርፉን በሚያሳድጉ የሪፎርም ስራዎች ላይ ላለፉት ስድስት ዓመታት ሲሰራ ቆይቶ በአሁን ጊዜ የአገልግሎት አሰጣጡን በማላቅ የዲጂታል ተቋም ለመገንባት ጥረት እያደረገ የሚገኝ መሆኑን አንስተው ስምምነቱ ይህን ጥረት የሚያግዝ ከመሆኑም ባሻገር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚታወቅበትን ብራንድ ለመገንባት ከአንጋፋው የኢተዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር የተደረገው ስምምነት ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ዘመናዊ ተቋም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተደራሽ መሆን እንዲችል፤የተጀመሩ የሪፎርም ስራዎችን የበለጠ እንዲያሳካና ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ ስራዎችን ለመስራት እንዲሁም ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠርና የሀገርን ገጽታ ለመገንባት ከዜና አገልግሎቱ ጋር ተደረገው የመግባቢያ ሰነድ የጎላ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምክትል ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ቤተልሄም አበባው በበኩላቸው ባለስስልጣን መስሪያ ቤቱ የተልዕኳችን አካል የሆነ ተቋም በመሆኑ ተቋሙ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ይህን መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመው ተከታታይ የሆኑ ዘርፉን የሚመለከቱ የይዘት ስራዎችን በመስራት ለማህበረሰቡ ተደራሽ ይደረጋል ብለዋል፡፡ ከስምምነት ሰነዱ የፊርማ ስነስርዓት በተጨማሪም የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የማኔጅመንት አባላት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል፡፡





