የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በትብብር ለመስራት ተስማሙ፡፡

ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በተሰጠው ሃላፊነት መሰረት የሲቪል ማህበራት ህግን እና የተቋቋሙበትን ዓላማ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ እንዲሁም የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸው ህግን በተከተለ መልኩ ለህዝብ ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ የቁጥጥርና የክትትል ስራዎችን እያከናዎነ የሚገኝ ሲሆን ይህንን ኃላፊነቱን በመወጣት ህግን ያልተከተሉ አካሄዶች እንዲታረሙ በማድረግ የሲቪል ማህበራት ዘርፍ የበለጠ ተኣማኒነትና ተቀባይነት ያለው ሆኖ በዘርፉ የተከናዎነው ሪፎርም ግቡን በተሟላ መልኩ እንዲመታና እንዲፀና ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ባለስልጣን መ/ቤቱ በአዋጁ አንቀፅ 6(16) እንዲሁም የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በአዋጅ 780/2005 እና በተቋቋመበት ደንብ እንደተመለከተው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራትን የማከናወን ስልጣንና ኃላፊነታቸው ለመወጣት በጋራና በትብብር ሲሰሩ የቆዩ ሲሆን የበለጠ ውጤታማ ትብብር ለማድረግ በማሰብ በዛሬው እለት የጋራ መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የጋራ ስምምነቱ ሁለቱ ተቋማት በህግ እና ዓለም አቀፍ መርሆዎችን መሰረት በማድረግ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የፋይናንስ እንቅስቃሴ ህግን የተከተለ እንዲሆንና የፋይናንስ ምንጫቸው ከህጋዊ ምንጭ አንዲሆን ለማድረግ በተለይም ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን መከላከል ላይ ግንዛቤ የማስጨበጥ፣ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጉ ማስቻል እንዲሁም ተገቢውን የቁጥጥርና የክትትል ስራዎችን ለማከናዎን የሚያስችላቸው እንደሆነ በውይይቱ ላይ በስራ ኃላፊዎቹ ተገልፆል፡፡
አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሪፎርም የተደረገው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ የበለጠ ውጤታማነቱ እየተጠናከረ እንዲሄድ ከባለድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ የትብብር ስራዎች መጠናከር የሚኖርባቸው መሆኑ በፕሮግራሙ ላይ ተጠቅሷል፡፡ የተቋማቱ ዋና ዳይሬክተሮች፣ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮችና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በመድረኩ ላይ ተሳትፈዋል፡፡ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎችን የመከላከል አስፈላጊውን ተግባራት እንዲያከናውኑ አገራት በዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ደረጃ በወጡ ስምምነቶች ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡
Click the button