የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኩሶ ኢንተርናሽናል (CUSO international) ጋር በመተባበር በወራቤ ዩኒቨርሲቲ በበጎ ፈቃድና በVMIS ዙሪያ ስልጠና ሰጠ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 በተሰጠው ስልጣንና ተግባር በጎ ፈቃደኝነትና በጎ አድራጊነትን ባህል ለማድረግ የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን ኩሶ ኢንተርናሽናል (CUSO international) ከተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ጋር በመተባበር በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡
ይኸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተውፊቅ ጀማል (PhD) እና አቶ ጀማል ሬድዋን የዪኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተርና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው የስራ ሃላፊዎችና ተማሪዎች በተገኙበት ተሰጥቷል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በጎ ፈቃደኝነትን ባህል ለማድረግና በማህበረሰቡ ውስጥ ለማስረጽ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመው የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን የሚመለከቱ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመስጠት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
ባለሰስልጣን መስሪያ ቤቱ የበጎ ፈቃድ መምሪያ በማዘጋጀትና ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረው የሚያስችል የፖሊሲ ማዕቀፍ እያዘጋጀ ሲሆን በተለይም VMISን በመጠቀም በጎ ፈቃደኞች ባሉበት ቦታ ሆነው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን የአሰራር ስርዓት ዘርግቶ ወደተግባር የገባ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ላይ VMISን በመጠቀም ተሳትፎ እንዲያደርጉ የሚያግዙ ስልጠናዎችን በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ሙያን መሰረት ያደረጉ የበጎ አድራጎት ስራዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ባህል እንዲሆኑ በማስቻል ማህበረሰቡ በተሻለ ሁኔታ ከበጎ አድራጎት ስራዎች ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የበጎ አድራጎት ዴስክ ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ሽልማት መርሻ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት የበጎ አድራጎት ስራ መሰረቱ ቤተሰብ እንደሆነና ከቤተሰብ የምናዳብረው ይህ መልካም ተግባር አድጎ ማህበረሰብንና ሀገርን የሚጠቅም እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡
በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የተሰጠው ስልጠና ትኩረቱን ያደረገው በበጎ ፈቃድ ጽንሰ ሃሳብና በVMIS የአጠቃቀም ስርዓት ላይ ሲሆን ስልጠናውን የሰጡት የሲቪል ማህበረሰብ ድጅቶች ባለስልጣን የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ አሉላ ሚሊዮን እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ማጎልበትና ትብብር ስራ አስፈጻሚ የበጎ ፈቃድ ማጎልበት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ ሽልማት መርሻና የበጎ ፈቃድ ማጎልበት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ጥላሁን ኩሳ ናቸው፡፡




