የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች በአማራ ክልል ከሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በባህር ዳር ከተማ ምክክር አድርገዋል፡፡ የውይይት መድረኩ በክልሉ የፋይናንስ ቢሮ በኩል የተዘጋጀ ሲሆን የቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ጥላሁን መሀሪ እና የክልሉ የተለያዩ የመንግስት ተቋማት አመራሮች እና በክልሉ በሰብዓዊ ድጋፍ እና በልማት ስራዎች ላይ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ድርጅቶች ተሳታፊ ሁነዋል፡፡
May be an image of 2 people and dais
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ቀዳሚ ተግባር የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ከመሆኑ አንፃር በግጭትና በተለያዩ ምክንያቶች ችግሮች በሚያጋጥሙበት ወቅት ከማንኛውም አካል በመቅደም ሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ እና የመልሶ ግንባታ ስራዎችን ማከናዎን እንደሚኖርባቸው በውይይቱ አጽንኦት ተሰጥቶት ቀርቧል፡፡ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢ ስራዎችን የሚያከናውኑ ሲቪል ማህበራት ችግሮች አጋጥመዋል በሚል ስራቸውን ሳያቆሙ ወይም ሳይቀንሱ ይልቁንም በበለጠ በማጠናከርና በማሳደግ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የአስቸኳይ ጊዜ ምላሾችን እያደረጉ መሆኑን በማንሳት ለዚህም ተንቀሳቀሶ ለመስራት የሚያስችል ሁኔታ ያለ መሆኑን አቅርበዋል፡፡ ሆኖም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዋፅኦ በስፋትም በተደራሽነትም መሻሻል የሚገባው መሆኑ እና ለዚህም ሲቪል ማህበራት ሃብት በማሰባሰብ ማህበረሰቡን ባሳተፈ መልኩ ስራዎችን መስራት እንደሚገባቸው ጥሪ ተላልፏል፡፡
በዚሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግና በዘላቂ ልማት ስራዎች ላይ በተለይም ትምህርት ቤት እና የጤና ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በማድረግ ከመቼውም ጊዜ በላይ መስራት እንዳለባቸው የባለስልጣኑ አመራሮችና የክልሉ የስራ ሃላፊዎች አፅንኦት ሰጥተው ገልፀዋል፡፡
የባለስልጣን መ/ቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የመንግስት ቁርጠኛ መሆንን አረጋግጠው ለማህበረሰቡ የሰብዓዊ ድጋፎችን በማድረግ እንዲሁም ዘላቂ ልማትና ሰላምን የሚያረጋግጡ ስራዎችን በማከናዎን ረገድ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በንቃት እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል፡፡ ባለስልጣን መ/ቤቱም ለዚህ ስኬት አስፈላጊውን የማስተባበር፣ የመደገፍና የመከታተል ሚናውን የሚወጣ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡