የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን የተቋሙን ሰራተኞች የንባብ ባህል ለማሳደግ እና የእርስ በእርስ ግንኙነትን ለማጠናከር በሚል የተጀመረው ተቋማዊ የንባብ ቀን ለ11ኛ ጊዜ በድምቀት ተካሂዷል፡፡
በዕለቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች እንዲሁም ከፌ.ደ.ራ.ል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
May be an image of 1 person and text
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ተቋማዊ የንባብ ቀንን የመሰሉ ከተቋማችን አልፎ ለሌሎችም ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ስራዎችን አጠናክሮ በመቀጠል አንባቢ ትውልድ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ የፍትህ ሚንስቴር ሚንስትር ደዔታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርኃን መርሃ ግብሩ ሳይቆራረጥ እዚህ በመድረሱ መደሰታቸውን ገልጸው መርሃ ግብሩ ለተቋሙ ሊጠቀስ የሚችል ትልቅ ተግባር በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በኩል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሶፎስ አፍሪካ መስራችና ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር ደስታ ሃሊሶ በፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሲሆን የተቋሙን ቤተ መጻህፍት ለማጠናከርና የርሳቸውንም ልምድና ተሞክሮ ለማጋራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በመርሃ ግብሩ ላይ በፌ.ደ.ራ.ል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የማረምና ማነጽ ተሃድሶ ልማት ዘርፍ የትምህርትና ስልጠና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ አዝመራው አብደታ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ከንባብ ጋር በተያያዘ ያሉ ተሞክሮዎች ያቀረቡ ሲሆን በተለይም ከታራሚዎች ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የእውቀት ማዕከላትንና ቤተመጻህፍትን በማደራጀት ረገድ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ተቋማዊ የንባብ ቀን ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየወሩ በተከታታይ የተለያዩ ሰዎችን በመጋበዝ የንባብ ተሞክሯቸውን እንዲያቀርቡና የተቋሙ ሰራተኞችም ያላቸውን ተሰጥዖ እንዲያሳድጉና የንባብ ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ በማድረግ ረገድ አስተዋጽዖ እያደረገ ያለ ተቋማዊ ፕሮግራም ነው፡፡