“የፍትህ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ለሚስተዋሉ ችግሮች መፍትሄ በማስቀመጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ያስፈልጋል” ክቡር ኤርምያስ የማነብርሀን (ዶ/ር):: የፍትህ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) ይህን ያሉት በዛሬው ዕለት የፍትህ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት የፍትህ ዘርፍ የአገልግሎት አሰጣጥን ማሻሻልን አላማው ያደረገ የፍትህ ዘርፍ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ፎረም የንቅናቄ መድረክ ላይ በተገኙበት ነበር።

May be an image of 5 people, newsroom, dais and text

የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 12 ላይ የመንግስት አሰራር ግልፅና ተጠያቂነት ባለበት መልኩ መሰጠት እንዳለበት ማስቀመጡን የገለፁት ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው በዚሁ መሰረት አገልግሎት አሰጣጡን ከመልካም አስተዳደር ፅንሰ ሀሳቦች ጋር የሚቆራኝ በመሆኑ ተጠያቂነት፣ አካታችነት፣ ግልፅና ቀልጣፋ በሆነ መልኩ አገልግሎት መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ አክለዋል።
ክቡር ሚኒስትር ዲኤታው ከፍትህ ዘርፍ ልዩ ባህሪያት አንዱ አገልግሎቱ በግል የማይሰራ መሆኑና የሚሰጡ አገልግሎቶችም ከተቋማቱ ብቻ የሚገኙ መሆናቸውን በሚገባ በመገንዘብ የሚስተዋሉ ችግሮችን አውቆ መፍታት በሚያስችል መልኩ ተፈጥሯዊ ሃላፊነትና ከፍተኛ ግዴታ ያለብን መሆኑን በመረዳት መስራት ይገባልም ብለዋል። አያይዘውም መልካም አስተዳደር በሀላፊዎች መልካም ፈቃድ ብቻ የተመሠረተ መሆን የለበትም ፤ ተቋማዊ መሆን አለበት ካሉ በኋላ በፍትህ ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቅንጅታዊ አሰራርን በመፍጠርና በማዳበር ተቋማዊ በሆነ መልኩ አገልግሎት ማግኘት የህዝቡ መብት መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት መንቀሳቀስ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ኡመድ ኡጁሉ በበኩላቸው ብልሹ አሰራርን የምንከላከለው የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣንና ቀልጣፋ በማድረግ ነው ሲሉ በፍትህ ዘርፉ የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት ምን መስራት አለብን ለሚለው ጥያቄ መልስ እየሰጡ መሄድና የሰው አስተሳሰብ ላይ መስራት ብሎም በግልም ሆነ በተቋም ለመፍትሄው ቁርጠኛ በመሆን መስራት ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ይህ ካልሆነ ግን የህግ የበላይነትን ለማስፈን ተጠያቂነት ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።
በፍትህ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥና አሰራር ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ የተዘጋጀውን የዳሰሳ ጥናት ያቀረቡት በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የስነ- ምግባርና ፀረ ሙስና መከታተያ ክፍል ሃላፊ ወ/ሮ ትዕግስት አቡዬ በፍትህ ዘርፍ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከሚስተዋሉ ችግሮች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው ሙስናና ብልሹ አሰራር መሆኑን ተናግረዋል።
አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል በርካታ የመፍትሄ አቅጣጫዎች የተቀመጡ ሲሆን ተቀባይነት ያለው አገልግሎት መስጠትና ዘላቂ ተጠያቂነት ያለው ስርአት መገንባት ብሎም የተጠናከረ የመልካም ስነ- ምግባር ስርአት እንዲገነባ ማድረግ ከተቀመጡ መፍትሄዎች ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው። የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የቀረበው የዳሰሳ ጥናት ትክክለኛውን ችግር ያመላከተ መሆኑን አንስተው የተነሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ለመፍታትም እያንዳንዱ ተቋም በሀላፊነት ወስዶ መስራት እንደሚጠበቅት አንስተው በተለይም የፍትህ ዘርፍ አካላት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን በማጠናከር በጋራ ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ገልፀዋል።