የዛሬ አራት ዓመት ገደማ በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀፅ 85 መሰረት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ወደ ስራ መግባት እንዲችል የመጀመሪያውን መስራች ጉባኤ የማዘጋጀት ኃላፊነት የነበረበት ተቋማችን ኮሚቴ በማቋቋም የመጀመሪያው የምስረታ መድረክ እንዲካሄድ በማድረግ ምክር ቤቱ በይፋ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ምክር ቤቱ ከተቋቋመባቸው ዋና ዋና ዓላማዎች መካከል የውክልና፣ የማማከር እና የእርስ በእርስ ቁጥጥርን ከማጎልበት አንፃር ወደ ስራ ቢገባና ውጤታማ ቢሆን ለኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ዘርፍ እድገት ከፍተኛ ብሎም ለህዝብ ተጠቃሚነት ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡ ምክር ቤቱ የሚመራበት መተዳደሪያ ደንብ አፅድቆ በይፋ ተቋቁሞ ወደ ስራ ከገባ በኋላ ባለፉት ዓመታት የተለያዩ ተግባራትን ያከናወነ መሆኑን ባለስልጣኑ ይገነዘባል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ እስካሁን የተከናዎኑ ተግባራት እንደ መልካም ስኬት በመውሰድ ከዚህ በላይ ላቅ ያሉ ስራዎችን ማከናዎን ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ምክር ቤቱ ነጻ፣ ገለልተኛ እና ውጤታማ መሆን የሚጠበቅበት ከመሆኑ አንፃር ሃላፊነቱን በጥንቃቄ፣ በአስተውሎት፣ በአርቆ አሳቢነት እና ገንቢ (constructive) በሆነ መልኩ መወጣት ይኖርበታል በማለት በዚህ መልኩ የሚንቀሳቀስ ምክር ቤት እንደ አገር መኖሩ ስራዎችን በዘላቂነትና በውጤታማነት በማበርከት አገርና ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ ያስችላል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ የምክር ቤቱ ፕሬዝደንት ዶ/ር ንጉሱ ለገሰ በበኩላቸው “ተቋም ለመገንባት በተከታታይ ጊዜያት ለሚመጡ አመራሮች የሚጸና መሰረት ለመጣል የተደረገው ጥረት ተቋማዊ ተብሎ ሊገለጽ ይሚችል ውጤት ነው። የተቋም ግንባታ የማያባራ ነው መሰረቱ ግን ህግ፣ ስትራቴጂ፣ የአሰራር ስርዓት፣ መዋቀር የመሳሰሉትን መዘርጋት ነውና ከዚያ አንጻር እንደ ምክር ቤት መልካም እርምጃ ታራምደናል” ሲሉ ገልጸዋል፡: ምክር ቤቱ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፣ የኦዲት ሪፖርቱን፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሪፖርት፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ላይ ገለጻ የአመራር ለውጥ እና ሪፖቶች ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።

