11ኛው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና የፌዴራልና የክልል የመንግስት ባለድርሻ አካላት መድረክ ተካሂዷል፡: በጉባኤው ላይ የአዲሰ አበባ ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይን ጨምሮ የፌደራል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የክልል ፋይናንስና ፍትህ ቢሮ ተወካዮችና ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸዉ ጉባኤዉ የድርጅቶቹን አፈጻጸም ለመገምገም፣ ክፍተቶችን በመለየት የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማስቀመጥ እና መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ እንደሚያግዝ ተናግረዋል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ እንዲጎለብት በማድረግ የህዝብና የአገር ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያደርገውን የክትትልና ድጋፍ ስራ የበለጠ የሚያስቀጥል መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህብረተሰቡን የላቀ ተጠቃሚነት በተሻለ ሁኔታ እንዲያረጋግጡ ለማድረግ የፌደራልና የክልል ተቋማት ትብብርና ቅንጅት አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡በጉባኤዉ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገር ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጾ እንዳላቸዉ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ሰፊ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ከንቲባዉ በዘርፉ በሚከናወኑ ስራዎች በግሉ ዘርፍ ከሚደረገዉ እንቅስቃሴ ከሚገኘዉ ገቢ ባሻገር የልማት አጋሮችን በማስተባበር በርካታ ስራዎች እንደሚከወኑ ጠቁመዋል። ከተማ አስተዳደሩ የሚሰራው ስራ ሰፊ በመሆኑም የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑንም ጠቁመዋል። የልማት አጋሮች በሚከናወኑ የልማት ስራዎች ላይ ሰፊ ሚና እንዳላቸዉ የተናገሩት አቶ ጃንጥራር፤ በከተማ አስተዳደሩ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚሠጣቸዉን አቅጣጫ መሠረት በማድረግ አብዛኛዎቹ ጥሩ እንቅስቃሴ እያደረጉ እንደሆነም ጠቁመዋል።

