በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በድንገተኛ አደጋ ለተጎዱ የህብረተሰብ ክፍሎች ከ 10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የእለት ደራሽ ድጋፍ ተደረገ። በፍትህ ሚኒስቴርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን አስተባባሪነት የሰዎች ለሰዎች ድርጅት (Menschen fűr Menschen) ከ 10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። የኢፌደሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ኤርሚያስ የማነብርሃን በአከባቢው በደረሰው ድንገተኛ የተፈጥሮ አደጋ ህይወታቸውን ባጡ ወገኖች የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን በመግለፅ በአከባቢው የተጎዱ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት ለመደገፍ ከሲቪል ማህበረሰቦች ጋር በትብብር እንደሚሠሩ ተናግረዋል።

የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ሀገር አቀፍ ተጠሪ አቶ ይልማ ታዬ በበኩላቸው በደረሰው ሰበዓዊ ጉዳት ድርጅታቸው ማዘኑን ገልጸው ድርጅታቸው ከ 10 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የእለት ደራሽ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል። አልባሳት ፣ የበቆሎ ዱቄት ፣ የምግብ ዘይት ፣ የህፃናት አልሚ ምግቦች ፣ አተር እና የንጽህና መጠበቂያ ቁሶቁሶችን ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ አስረክበዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ለተጎጂዎች የሚሆን 300 ሺህ ብር በዞኑ በተከፈተ አካውንት እንዳስተላለፈ ገልጸዋል። የክልሉ ፍትህ ቢሮ ፣ የሰዎች ለሰዎች ድርጅት እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተፈራርመዋል። በሰዎች ለሰዎች ድርጅት የተደረገው ድጋፍ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖች ለባሰ ሰበዓዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ የአንድ ወር ቀለብ መሆኑ ተገልጿል። ድጋፉን የተረከቡት ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጂነር ዳግማዊ አየለ የፍትህ ሚኒስቴርና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ድጋፉን በማሰተባበራቸው አመስግነዋል። አክለውም የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ላደረገው ሰበዓዊ ድጋፍ በዞኑ ህዝብ ስም አመስግነዋል።

