ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነት ባህልን ለማዳበር ለአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በአዋጅ 1113/2011 በተሰጠው ሀላፊነት መሰረት የበጎ ፈቃድና በጎ አድራጊነት ባህልን በህብረተሰቡ ውስጥ ለማስረጽ እና ውጤታማ ለማድረግ ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በጋራ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል።
በስልጠናው ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ለሰልጣኞች እንዳሉት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በህብረተሰቡ በእለት እለት ኑሮው ውስጥ ባህል መሆን እንዳለበት በማንሳት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካዊ ውስጥ በተለይ ደግሞ በስነ ምግባር የታነፀ፣ ህግና ስርዓትን የሚከተል፣ ማህበረሰቡን የሚያከብር፣ አገሩን የሚወድ ለሰዎች መልካም ነገርን በማድረግ የሚረካ ትውልድን የመፍጠር አቅም እንዳለው ገልፀዋል፡፡
በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ የተሰማራ ሰው መጥፎ ነገሮችን ከማድረግ የተቆጠበ ነው ያሉት ም/ዋና ደይሬክተሩ የሀሳብ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን በንግግርና በውይይት ለመፍታት የሚጥር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ሌላው እንደምሳሌ ያነሱት በመንግስት የተጀመሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እንደአርአያ በመውሰድ ተጠናክረው በህብረተሰቡ እንዲሁም በሲቪል ሶሳይቲው ውስጥ መሰራት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡
በመጨረሻም ባለስጣን መስሪያ ቤቱ በጎ አድራጊዎች የሚገናኙበት ፕላት ፎርም (VMIS) አዘጋጅቶ ወደስራ መግባቱን እንዲሁም ሌሎች ስራዎችም እየተከናወኑ መሆኑን አንስተው በዩኒቨርስቲው በበጎ ፈቃደኞች እየተከናወኑ ያሉ ስራዎችን በማድነቅ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱም ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በዩኒቨርስቲው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ 20/25 የተባለ የበጎ አድራጎት ድርጅት እያከናወነ ያላቸውን ስራዎች አቅርቧል፡፡
ከሰሯቸው ስራዎች ውስጥ አዲስ ተማሪዎችን ወደ ዩንቨርስቲው ሲመጡ አቀባበል ማድረጉ እና በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲግባቡ፣ የአረጋውያን መንከባከቢያ ቤቶችን እንዲሁም በአዳማ የሚገኙ ሌሎች ማህበረሰቦችን በመጎብኘት የምክር አገልግሎት በመስጠት የዜግነት ሚናውን እየተወጣ መሆኑን አቅራቢዋ ተናግረዋል።