May be an image of 5 people and people studying

ምክር ቤቱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓትን (Self-regulation scheme) ማጠናከር ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ምክረ ሃሳብ ቀረበ፡፡
በምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ የተመራ የባለስልጣን መ/ቤቱ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በመገኘት የምክር ቤቱን ቢሮዎች የጎበኘ ሲሆን በጋራ ጉዳዮች ዙሪያ ደግሞ ከምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በተደረገው ውይይት ምክር ቤቱ ያከናዎናቸው ተግባራት አበረታች መሆኑን በማንሳት በቀጣይ ምክር ቤቱ በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት በበለጠ መልኩ እንዲወጣ የሚያስችል ጥረት ማድረግ እንደሚገበ የተጠቆመ ሲሆን ለዚህም ያላፉት ዓመታትን አፈፃፀምን በጥልቀት በማየት ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸውን ማስቀጠል እንዲሁም መሻሻል ያለባቸውን ደግሞ ማስተካከል ተገቢነት ያለው አካሄድ መሆኑን ም/ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ምክር ቤቱ ነፃ፣ ገለልተኛ እና ለህዝብና ለአገር ጥቅም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ የሚያስችል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ በመገንባቱ ሂደት ላይ ከፍ ያለ ሚና ያለው እንደመሆኑ መጠን አዋጅ ቁጥር 1113/2011 በሚደነግገው አግባብ በዘርፉ የእርስ በእርስ የቁጥጥርና አስተዳደር ስርዓት እንዲዘረጋ በልዩ ትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተው የስነ-ምግባር ደንቡን በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ በቀጣይ በትኩረት ሊሰራበት የሚገባ መሆኑ ላይ ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በማያያዝ የተጓደሉ አመራሮችን ለማሟላት የሚደረግ ጥረት እንዲሁም በቀጣይ የሚካሄዱ የምክር ቤቱ ጉባኤዎችን በህግ የተሰጡትን ተግባራት በመፈፀም የሚያስችል ቁመና ያለው ምክር ቤት ለመፍጠር በሚያስችል መልኩ ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንዲከናዎኑ ማድረግ ጠቀሜታው ጉልህ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ም/ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መ/ቤቱ ከምክር ቤቱ ጋር ህግና መርህን መሰረት ባደረገ መልኩ ተባብሮ መስራቱን እንደሚያጠናክር እንዲሁም ተገቢውን ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን በንግግራቸው አረጋግጠዋል፡፡
የምክር ቤቱ ተ/ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሐና ወ/ገብርኤል እና የምክር ቤቱ የስራ ኃላፊዎች የምክር ቤቱን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ሃሳቦችን የሰነዘሩ ሲሆን በቀጣይም በባለስልጣኑና በምክር ቤቱ መካከል የጋራ በሆኑ ዘርፋዊና አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቋሚ የሆነ የውይይት መድረክ ቢፈጠር ጠቀሜታ እንደሚኖረው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1113/2011 አንቀፅ 2(11) እና አንቀፅ 85 መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በምክር ቤቱ አማካኝነት ራሳቸውን ለማስተዳደር በፈቃዳቸው በሚያወጡት የሥነ ምግባር ደንብ የሚመራ አስገዳጅ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ሥርዓት መዘርጋት እንደሚገባው እና አተገባበሩንም በሁሉም ድርጅቶች ተሳትፎ የሚመራው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በቅርበት እንደሚከታተል ተደንግጓል፡፡