የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ፋይናንስ ቢሮ የመንግሥትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች 3ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ አካሄደ፡፡

“መተባበራችን ለዕድገታችን” በሚል መሪ ሀሳብ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የመንግስትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት 3ኛ ዙር የጋራ ምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡
በምክክር መድረክ ላይ ተገኝተው መድረኩን በይፋ ያስጀመሩት የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ እንደተናገሩት የሲቪል ማኅበረሰብ መንግሥትን በማገዝ ለህብረተሰቡ መሠረታዊ የሆኑ ነገሮች በመሥራት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ ገልፀው በዘንድሮው ብቻ ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ በማውጣት እየደገፉ ይገኛሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ርዕሰ መስተዳድሩ መተባበር፣ መተጋገዝ፣ መረዳዳት ካለ የማይፈታ ጥያቄ እንደሌለ የገለጹ ሲሆን እነዚህ ድርጅቶች በክልላች የሚሠሩ የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ለሚያደርጉት ርብርብ አመስግነው የጀመሩትን ፕሮጀክቶችን አጠናክሮ እንዲያስቀጥሉ እና ለሚያስፈልጋቸው ድጋፍ ሁሉ የክልሉ መንግስት ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሃገር የሚያደርጉት አስተዋጽኦ እንዲጎለብት በፌደራልና በክልል በየደረጃው ያሉ የመንግስት ተቋማት ተገቢውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ቅንጅትና ትብብር ሊፈጥሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ተቋማቸውም ዘርፉ የበለጠ እንዲጎለብት እና የሃገርንና የህዝብን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ጠንካራ የክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የድጋፍ ስራዎችን በማከናወን የተጀመረውን የሪፎርም ስራ አጠናክሮ የሚያስቀጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አራርሶ ገረመሁ እንደተናገሩት የሲቪል ማኅበረሰብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሆነ ገልፀው 79 የሲቪል ማኅበረሰብ በ150 ፕሮጀክቶች ላይ ተሠማርተው ለመንግሥትና ለሕብረተሰቡ በከፍተኛ ደረጃ አጋዥ የሆኑተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በመቀጠልም ይህ የጋራ መድረክ የተሠሩ ሥራዎችን የሚገመገሙበት እና ለወደፊት የበለጠ ለመሥራት ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮች ተለይተው ለመስራት የጋራ ስምምነት የሚደረስበት እንደሆነ አመላክተዋል።