የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በሁለንተናዊ ልማት፣ በዴሞክራሲ ፣ የአገርን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ እና ህዝብን በተጨባጭ የሚጠቅሙ ስራዎችን በመስራት የሚመዘኑበት ወቅት መሆኑ ተገለጸ፡፡

ዘጠነኛው የኢፌዴሪ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣ የክልል እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት ጉባኤ በጂማ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በጉባኤው ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ መለስ ዓለሙ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ ሚኒስትር እንደተናገሩት መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በሁለንተናዊ መልኩ የበለፀገች አገር ለመገንባት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የሪፎርም ስራ ካካሄደባቸዉ መስኮች አንዱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚመለከት መሆኑን አንስተው ይህም የሆነበት ዋናዉ ምክንት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለአገራችን የልማትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ከፍተኛ ሚና የሚጫዎቱ መሆናቸውን በማመን ነዉ ሲሉ ገልጸዋል፡፡
መንግስት ላለፉት ዓመታት በዘርፉ ሰፊ የፖሊሲ፣ የህግ እና የተቋማዊ ሪፎርሞች እንዲካሄዱ አድርጓል ያሉት ሚኒስትሩ ከለዉጡ በፊት እንደፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉ የሲቪክ ምህዳሩም በመጥበቡ ምክንት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለሀገር ልማትና ዴሞክራሲ መወጣት የሚጠበቅባቸውን ሚና በሙሉ አቅማቸዉ መወጣት አንዳይችሉ አድርጓቸው ቆይቷል ብለዋል፡፡
አቶ ሳምሶን ቢራቱ የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት አሁን በደረስንበት ደረጃ ዘርፉ ከህዝብ ተጠቃሚነት አኳያ ትርጉም ያለው አስተዋፅኦ ማድረግ የሚገባው ወቅት ላይ እንደምንገኝ ገልጸው ይሄንኑ ውጤት ታሳቢ ያደረገ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ድጋፍ ማድረግ ከመንግስት አካላት ይጠበቃል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በሁለንተናዊ ልማት፣ በዴሞክራሲ ፣ የአገርን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ እና ህዝብን በተጨባጭ የሚጠቅሙ ስራዎችን በመስራት የሚመዘኑበት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው በመግለጽ በቀጣይም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ የተጠናከረ ክትትል እንዲሁም የድጋፍ ስራዎች የሚከናዎኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ጉባኤው በቀጣይ ከሲቪል ማህበራት ዘርፍ የሚጠበቀውን ተጨባጭ ውጤት ለማሳካት ትኩረት ያደረገ ቅንጅት በመፍጠር ሂደት ከፍተኛ አቅም መሆኑን አንስተው ይህ ከመንግስታት ግንኙነት ጋር በተያያዘ በአገራችን ለሌሎች ሞዴል መሆን የሚችል የጋራ ጉባኤ ሳይቋረጥ እንዲቀጥል ለማድረግ ተቋማችን ይሰራል ብለዋል፡፡
የጅማ ዞን ም/አስተዳዳሪ ለጉባኤተኛው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር እና አቀባበል አድርገዋል፡፡