የሲቪል ማህበራትና የመንግስት አካላት ትስስር ለተሻለ የህጻናትና የሴቶች መብቶች ጥበቃ በሚል ርዕስ ውይይት ተካሄደ፡፡

በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና በጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ (JFA- PFE) ትብብር በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት እና ሴቶችን እና ህፃናትን ማዕከል አድርገው ከሚሰሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የውይይት መድረኩን የከፈቱት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የሴቶችን እና የህጻናትን ተጠቃሚነት ለማጎልበትና የተሻለ የሴቶች እና የህጻናት መብቶች ጥበቃ ለማድረግ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚሰሩ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተቀራርበው ቢሰሩ ትልቅ ለውጥ ማምጣት የሚችሉበት አጋጣሚ ከመኖሩም ባሻገር ለሀገር ልማትና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ላይ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የውይይት መድረኮች መኖራቸው ለሚፈጠረው ትስስር አቅም የሚፈጥር ከመሆኑም ባሻገር የሚፈጠሩ ትስስሮችን ዓላማ በሚገባ በመገንዘብ ትስስሮችን ለማጠናከር እና ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ሥራዎችን ለማከናወን አጋዥ እንደሚሆኑ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መሰል ትስስሮችን በመፍጠር የውስጥ ቁጥጥር፣ ግልጽነትና ተጠያቂነትን አጠናክረው የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችን ለመደገፍ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ትስስሮች ስለሚኖራቸው ጠቀሜታ እና ስለሚያጋጥሙ ተግዳሮቶች፣ የትስስር ዓይነቶችና እና ትስስሮችን በሚመለከት ያሉ የህግ ማዕቀፎች ላይ ያተኮረ ሰነድ ያቀረቡ ሲሆን ትስስር መፍጠር እና በትስስር መንቀሳቀስ ያሉትን ውስን ሃብቶች ለመጠቀም እንዲሁም በሴክተሩ ትርጉም ያለውና የሚታይ ለውጥ እንደ ሀገር ለማምጣት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ትስስር ለመፍጠር የሚያስችሉ አማራጮችን በዘርፉ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተነጋግረው በሚስማሙበት አማራጭ ላይ ትስስሩን በመፍጠር ሴክተሩን ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ ትስስር መፍጠር በራሱ እንደ ትልቅ ግብ ሊታይ እንደማይገባ ያነሱት ምክትል ዋና ትስስሩን ማጠናከርና ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት፤ በተለይም ውስጣዊ አቅምን ማጎልበት እና ትስስሩን ዘመኑን የዋጀ ዲጂታል ትስስርን መፍጠር ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚኖርበት አንስተዋል፡፡
የጀስቲስ ፎር ኦል የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ከፍተኛ ባለሙያ “Networking with digital resources” በሚል ርዕስ መነሻ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ የውይይት መድረኩ በጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ የስልጠና ማዕከል ለሁለት ቀናት የተካሄደ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ትስስር ስለሚፈጥሩበት ሁኔታ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ የሴቶችና ህጻናትን መብቶች ጥበቃ በሚመለከትም ስልጠና ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ትስስር ለመፍጠር የሚያስችል ጋራ አስተባባሪ ኮሚቴ ተመርጦ መድረኩ ማጠቃለያውን አድርጓል፡፡