ለተከታታይ 12 ቀናት ሲሰጥ የቆየው መሰረታዊ የምልክት ቋንቋ ስልጠና ተጠናቀቀ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሄራዊ ማህበርና ከኤል ኤም ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር “እጆች ይናገራሉ፤ አይኖች ያዳምጣሉ” በሚል መሪ ሀሳብ በተቋሙ የተለያዩ የስራ ክፍሎች ስር ለሚሰሩ 20 ባለሙያዎች ለ12 ቀናት ሲሰጥ የቆየውን የመሰረታዊ የምልክት ቋንቋ ስልጠና በዛሬው እለት አጠናቋል፡፡
በሰልጣኞቹ የምርቃት ስነስርዓት ላይ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱን ከፍተኛ ሃላፊዎችና ከኤል ኤም ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
በዕለቱ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ ሁሉን አቀፍ እንዲሆንና ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹ ሲሆን ተቋሙ በሁለተኛው የትራንስፎርሜሽን ምዕራፍ እንደመገኘቱ ይህ ስልጠና ተገልጋዮችን አካታች በሆነ መልኩ ለማገልገል ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ሰልጣኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ ስኬታማ ለውጥ በማምጣታቸው መደሰታቸውን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ፋሲካው የተቋሙን አገልግሎት አሰጣጥ ሊያሻሽሉ የሚችሉ መሰል ስልጠናዎች እንደሚሰጡም አክለው ገልጸዋል፡፡
የኤል ኤም ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ ፕሮግራም ኃላፊ አቶ ምንባለ ጌታቸው በበኩላቸው ድርጅታቸው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር ይህን ስራ መስራት በመቻሉ በጣም ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው ወደፊትም ወደፊትም መሰል ትብብሮችን በመፍጠር በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡
በምረቃት ስነስርዓቱ ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በምክትል ዋና ዳይሬክተሩ የተሰጠ ሲሆን ለዚህ ስልጠና መሳካት አስተዋጽዖ ላደረጉ ተባባሪ አካላትና አሰልጣኞችም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡