ኮድ ኢትዮጵያ ለባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ የተለያዩ መጽሀፍቶችን በስጦታ አበረከተ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተቋማዊ ለውጥን ከማጠናከር አንጻር እንዲሁም የሰራተኞችን የንባብ ባህል ለማጎልበት ወራዊ የንባብ ቀን በማዘጋጀት ለተከታታይ 5ዙር አካሂዷል፡፡
ኮድ ኢትዮጵያም በአንደኛው ዙር የንባብ ቀን በገባው ቃል መሰረት ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ሶስት መቶ መጽሀፍትን ለተቋሙ አስረክቧል፡፡
በርክክቡ ላይ የተገኙት የኢፌዲሪ የፍትህ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ የማነ ብርሃን የሰው ልጅ ለመኖር ምግብ እንደሚያስፈልገው ሁሉ አዕምሮውን ለማጎልበት ንባብ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ተቋሙ የጀመረው ስራ አበረታች እና ለሌሎችም ምሳሌ የሚሆን ነው ብለዋል፡፡
የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንዳሉት ይህ የንባብ ቀን የተቋማዊ ለወጥ አንዱ አካል መሆኑን በመግለጽ በሰራተኞች ላይ የአንድነትን መንፈስን ለማዳበር ፣ እርስበዕርስ ለመተዋወቅና የቡድን መንፈስን ለማጠናከር በማሰብ የንባብ ቀን ለማዘጋጀት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
አክለውም በመጀመሪያ ዙር የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተጋበዙ መሆኑን እና በፕሮግራሙ ላይ የተለያዩ መጽሀፍቶችን ለመስጠት ቃል የገቡ መሆናቸውን በመግለጽ ከዚ ውስጥም ኮድ ኢትዮጵያ በገባው ቃል መሰረት ሶስት መቶ የተለያዩ ይዘት ያላቸውን መጽሀፍት ለተቋማችን በማምጣቱ በተቋሙ ስም ለማመስገን እወዳለው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የንባብ ባህልን በተቋሙ ለማዳበር እና ቀጣይነት እንዲኖረው ለማድረግ የተቋሙ ቤተመጻህፍት አገልግሎት እንዲጀምር ማድረጉ ይታወቃል፡፡