CSO-IFA Working group ተመሰረተ፡፡

ዛሬ በአዲስ አበባ ኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል በነበረው ስብሰባ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል ሃገር ከመሆኗ ጋር ተያይዞ እና በዚህ ረገድ የሲቪል ማበረሰብ ድርጅቶች ሚናን በተመለከተ ውይይት ተደርጓል፡፡
በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አምባሳደር ምስጋኑ ረታ እንደገለጹት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የማይተካ ሚና እንዳላቸው በመግለጽ የኢትዮጵያ ጥቅም በሚያስከብሩ ጉዳዮችና በሃገሪቱ የገጽታ ግንባታ ላይም በሃላፊነት ሊሰሩ ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በበኩላቸው ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የአገርና ህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ ተግባር ለማከናወን የሚቋቋሙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ መድረክም የኢትዮጵያ አምባሳደር የመሆን ድርብ ሃላፊነት ያለባቸው ስለሆኑ የአገራችንን የውጭ ግንኙነትና ዲፕሎማሲ ድሎችን፣ እድሎችን እንዲሁም ተግዳሮቶችን በውል በመረዳት፣ ቀጠናዊ፣ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ አውዶችን በመገንዘብ እንዲሁም በመረጃና በእውቀት ላይ በመመስረት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ አኳያ የዛሬው መድረክ ዋነኛ አላማዎች በቅርቡ አገራችን በዓለም አቀፍ የመንግስታት ግንኙነት ከፍተኛ ተፅእኖ እየፈጠረ ያለው የሃያላን ስብስብ የሆነውን ብሪክስ ፕላስ አባል መሆን ከመቻሏ ጋር ተያይዞ ዝርዝር ጉዳዮችን በመነጋገር ግንዛቤን መፍጠር እንዲሁም በቀጣይም በቋሚነት የውጭ ግንኙነት ተቋማት ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተለያዩ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ የሚወያዩበት ማዕቀፍ መዘርጋት ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በዚህ አጋጣሚ አገራችን የብሪክስ ፕላስ አገራት አባል መሆን መቻሏ በታሪክ ፊት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው እና በኢትዮጵያ የምትንቀሳቀሱ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ባስተላለፉት መልዕክት መስሪያቤታችን ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውጤታማ ስራ በማከናዎን በአገር ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና መጫዎት እንዲችሉ ከተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማት ጋር ስትራቴጅክ የሆነ የትብብርና ቅንጅት ማዕቀፍ ፈጥረው እንዲሰሩ ለማድረግ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር እየሰራ ሲሆን ይሄው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡