በአዲስ አበባ 10ኛው የመንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የጋራ የምክክር መድረክ ተካሄደ፡፡

በከተማ መስተዳድሩ 311 ድርጅቶች 352 ፕሮጀክቶችን ተፈራርመው እየሰሩ እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡
የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ አቶ አብዱልቃድር ሬድዋን እንደገለጹት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በከተማው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ላይ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው በመግለጽ የመድረክ ዓላማ በዘርፉ የተገኙ ጠንካራ ጎኖችን ለማጎልበትና ያጋጠሙ ችግሮችን ለመገንዘብና በጋራ ለመፍታት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በማጠቃለያ ንግግራቸው እንደገለጹት እንደዚህ አይነት ቋሚ መድረኮች በጣም አስፈላጊ እና በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የእርስ በእርስ ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
የበለጸገች ኢትዮጵያን በመገንባት ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዘርፉ በሚፈጠሩ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ እና ሃሳብ አመንጪ መሆን እንደሚገባቸው አንስተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ህግና ስርዓትን አክብረው እንዲሰሩ፣ ሃገራዊ ፍቅር እንዲኖራቸው ውስን ሃብትን በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ አደራ እላለሁ ብለዋል፡፡
በመድረኩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በከተማ መስተዳድሩ በማህበራዊና በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ያከናወኗቸው ተግባራት የቀረበ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አመሰራረት፣ተግባርና ሃላፊነት እንዲሁም ያከናወናቸውን ተግባራት ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡