በዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ የተመራ ልዑካን ቡድን በትግራይ ክልል የተለያዩ አከባቢዎች አክሽን አጌንስት ሀንገር (Action against Hunger) የሚሰራቸውን ስራዎች ተመልክቷል፡፡

በትግራይ ክልል አክሽን አጌንስት ሀንገር (Action against Hunger) የተባለው የውጭ ግብረሰናይ ድርጅት እያከናወነ ያለውን ስራ ምልከታ ያደረገ ሲሆን ድርጅቱ በትግራይ ክልል በአስራ ሶስት ወረዳዎች ኒውትሪሽን ፣በውሃ፣ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ላይ ይንቀሳቀሳል፡፡
ድርጅቱ ካከናወናቸው ተግባራት መካከል በአቢ አዲ ጤና ጣቢያ በወሊድ ጊዜ የመቀንጨር ዕክል ላጋጠማቸው ህፃናት የተለያዩ የአልሚ ምግቦች ድጋፍ እና በእናቶች ጤና ዙርያ እየሰራ ያለውን ተግባር ቡድኑ ተመልክቷል ፡፡
በምልከታውም ወቅት የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር አቶ ወልዳይ መረሰ እንደተናገሩት ይህ ጤና ጣቢያ ለአርባ ሺህ የማህበረሰብ ክፍሎች አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም መሆኑን ገልጸው በነበረው ወቅታዊ ሁኔታ አገልግሎቱ ተቋርጦ መቆየቱን እና አሁንም አገልግሎቱ ቢጀመርም የመድሃኒት አቅርቦት ችግር እያጋጠማቸው መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአክሽን አጌንስት ሀንገር (Action against Hunger) ጤና ጣቢያው ወደ አገልግሎቱ እንዲመለስ አያደረገ ያለው ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው ይህም ድጋፍ በቀጣይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንፈልጋለን ብለዋል ፡፡
በምልከታው ላይ የነበሩት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንደተናገሩት በጤና ባለሙያዎችና ሃላፊዎች የተነሱት ችግሮች እንደ ተቋማችን ወስደን ማድረግ ያለብን ድጋፎች ሁሉ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል ፡፡
ሌላኛው የአክሽን አጌንስት ሀንገር (Action Against Hunger) ፕሮጀክት በትግራይ ክልል ዓድዋ፣ዓዲግራት፣አክሱም እና ሽረ ከተማ የሚገኘው የካሽ ዲስትርቢዩሽን ፕጀክት ምልከታ የተደረገ ሲሆን ይህም ከተለያዩ አከባቢዎች ለተፈናቀሉ የማህበረሰብ ክፍሎች በካሽ ገንዘብ ለ( ሁለት መቶ አርባ ስድስት ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ስምንት 246988) ተፈናቃዮች፣ከስደት ተመላሾችና ችግረኛ ነዋሪዎች ድርጅቱ ባዘጋጀው መመርያና መመዘኛ መስፈርት መሰረት አምስት መቶ ሚሊዮን ብር እንደየ ቤተሰብ ብዛታቸው ተደራሽ እያደረገ እንደሚገኝ የፕሮጀክት አስተባባሪ ሃላፊው አቶ አለማየሁ አብረሃ ተናግረዋል ፡፡
በመጨረሻም የባለስልጣን መስርያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በሰጡት አስተያየት አክሽን አጌንስት ሀንገር (Action against Hunger) እያደረገ ያለው ድጋፍ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረው ይሁን እንጂ የሚደረጉት ድጋፎች ቀጣይነት ያለው እና የማህበረሰቡን ህይወት በሚቀይር መልኩ መሆን ይገባዋል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡