ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና የሚመለከታቸው ሁሉ የመንገድ ደህንነት ጉዳይ ሚመለከታቸው በመሆኑ በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ተጠቆመ፡:

ይህ የተባለው ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ እንደርሳለን በሚል መሪ ቃል በመንገድ ደህንነት ላይ ትኩረቱን አድርጎ በኢትዮጵያ መንገድ ደህንነት ማህበር በተዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ ነው፡፡ በመድረኩ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላን ጨምሮ የመንገድ ደህንነትና ፈንድ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ጀማል አባሶ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተገኝተዋልለ፡፡
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደገሉጹት የትራፊክ አደጋ በየአመቱ በረካታ ቁጥር ያለው ህዝብ እና ሀብት እያወደመ ይገኛል፡፡ ይሀንን አደጋ ለመቀነስ የመንገድ ደህንነትን በሚመለከት የሁሉንም ርብርብ የሚጠይቅ ነው፡፡ በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ በጎ ፈቃደኞችና የሚመለከታቸው ሁሉ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው በንግግራቸው አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
አክለውም ከጳጉሜ እስከ ጳጉሜ መድረስ ብቻ ሳይሆን ተከታታይነት ያለው ስራ መስራትና በተለይም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በመንገድ ደህንነት ላይ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ልምድና ተመክሮዎችን በማምጣት ግንባር ቀደም ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጠቁሟል፡፡
በእለቱ የመንገድ ደህንነትን በሚመለከት የፓናል ውይይት የተደረገ ሲሆን የኢትዮጵያ መንገድ ደህንነት ማህበር ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመንገድ ደህንነት ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችል የጋራ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ማህበሩ በመንገድ ደህነት ላይ አስተዋጽዖ ላበረከቱ አካላት እውቅና የሰጠ ሲሆን የመንገድ ደህንነትን በሚመለከት ግንዛቤ የሚፈጥሩ እና የሚያስተዋውቁ አንባሳደሮችንም ሾሟል፡፡