ጳጉሜ 3 የበጎነት ቀን ፡፡

የበጎነት ቀን “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ቃል የፓናል ውይይት በማድረግ፣ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና በጎ አድራጊ ግለሰቦች እውቅና በመስጠት ተከብሯል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ከሰላም ሚኒስቴር እና ከኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የበጎነት ቀንን “በጎነት ለሀገር” በሚል መሪ ቃል በሃይሌ ግራንድ ሆቴል ተከብሯል፡፡ በዝግጅቱ ላይ የፌደሬሽን ምክርቤት ም/አፈ ጉባዔ ወ/ሮ ዛህራ ሁመድን ጨምሮ ሚንስትሮችና የተለያዩ ተቋማት ኃላፊዎች እንዲሁም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተወካዮችና በጎ አድራጊ ግለሰቦች ተገኝተዋል፡፡
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚንስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) የበጎነት ጥቅሙና ትሩፋቱ ለራስ መሆኑን ጠቅሰው በጎነት ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ያለው ከበጎ ልቦናና ከቅን ልቦና የሚመነጭ በነጻ የሚሰጥ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ አያይዘውም የበጎነት አስተሳሰብ ሀገርና ህዝብን ማገልገል ትለቅ ክብር መሆኑን ያነሱት ሚንስትሯ ሰዎች የሚሰሩት የበጎ አድራጎት ስራ ከውስጣቸው ካለ እሴት ጨምረውበት ለሀገርና እድገት እና ለህብረተሰብ ለውጥ የሚያውሉበት በምላሹም ደስታ እና ጠቃሚ የህይወት ተመክሮ የሚገኝበት መሆኑን አውስተዋል፡፡
የሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ብናልፍ አንዷለም በጎነት በመናገር ሳይሆን በተግባር የሚገለጽ ከሰዎች ሰብዓዊነትና የውስጥ ተነሳሽነት የሚመነጭ ቅኖች፣ ልበ መልካሞች የሚያደርጉት ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በጎ ሰዎች በጎ ተግባር ሲፈጽሙ ትመለከታላችሁ እንጂ ሲያወሩት አታዩም ያሉት ሚንስትሩ በጎነት ሲተገበር ነገ የሚገኘውን በማሰብ ሳይሆን እንዲሁ በነጻ ተግባር የሚደረግ ነው ብለዋል፡፡
በመድረኩ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት ዶ/ር ብርኃነመስቀል ጠና ለፓናል ውይይቱ የሚሆን መነሻ ጽሁፍ ያቀረቡ ሲሆን በሀገር አቀፍ ደረጃ በበጎነታቸው ምስጉን ለሆኑ ግለሰቦችና ድርጅቶች የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት ተበርክቷል፡፡