የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በሆለታ ኢፈ ቦሩ ቱሉ ሀርቡ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለ3ኛ ጊዜ የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር አከናወነ።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመሆን ሀገር በቀል እጽዋትንና ለምግብነት የሚውሉ ከ3000 በላይ ችግኞችን “ነገን ዛሬ እንትከል!” በሚል መሪቃል ተክለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ በማኖር ስነስርዓቱ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱን ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎችና የሆለታ ከተማ አስተዳደር የግብርና ጽህፈት ቤት ሃላፊዎች እንዲሁም የባለስልጣን መስሪያቤቱ ሰራተኞችና ከተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በመርኃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት በአረንጓዴ ልማት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚ ድህነትን በዘላቂነት እንደሚቀርፍ ገልጸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሀገራዊ ጥሪውን ተቀብሎ ልክ እንደሁልጊዜው በሁለተኛው ምዕራፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካባቢን ከመጠበቅ ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎችን በተከታታይ ለ3ኛ ጊዜ በመትከል ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
አክለውም የችግኝ ተከላው በትምህርት ቤት ውስጥ መከናወኑ ትልቅ መልዕክት እንዳለው ገልጸው ትምህርት ቤት የነገን ትውልድ የሚቀረጽበት እንደመሆኑ ትልቅ ትርጉም አለው ብለዋል፡፡
ሆለታ ግብርና ጽህፈት ቤትን ወክለው የተገኙት አቶ በርሲሳ በበኩላቸው ችግኞችን መትከል ብቻ ግብ አይደለም፤ ችግኞችን መንከባከብ ተገቢ መሆኑን አንስተው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እዚህ ድርረስ መጥቶ የችግኝ ተከላን በማከናወኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በስሩ ከሚገኙ ሰራተኞች ጋር ለተከታታይ ሶስት ዙር በርካታ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎችን የተከለ ሲሆን ከፍትህ ሚንስቴር ተጠሪ ተቋማት እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች ላይ በስፋት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡