የሶስቱ አካላት አጋርነት ለሌላው ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፣የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት እና የCSSP2 አጋርነት ለሌሎች ተምሳሌት እንደሚሆን ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ገልጸዋል፡፡
ለዘርፉ እድገት፣ግልጸኝነትና ተጠያቂነት በርካታ ውጤታማ ስራዎችን በጋራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን ገልጸው በቀጣይም እንዲህ አይነት ትብብር እና አጋርነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ከ CSSP2 ጋር በጋራ በመሆን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 መሰረት በማድረግ ስምንት የጸደቁ መመሪያዎችን በማሳተም ዛሬ ለባለስልጣን መስሪያቤቱ አስረክበዋል፡፡
በርክክብ ስነስርዓቱ ላይ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በዘርፉ በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር ስርዓት መዘርጋት አንዱ የተቋሙ ቁልፍ ተግባር መሆኑን አንስተው ይህ መመሪያም ባለድርሻ አካትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተረድተው ተግባራዊ ለማድረግ ያግዛል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ውጤታማ ዘርፍ ለመፍጠር በመተባበር መስራትና ጠንካራ ተቋም መገንባት ያስፈልጋል ያሉት ም/ዋና ዳይሬክተሩ በዚህ ሂደት ምክርቤቱ እና CSSP2 በርካታ ስራዎችን ሰርተዋል ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክርቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ መለሰ በበኩላቸው ከCSSP2 በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ አስራ ሁለት ሺህ ኮፒ መዘጋጀቱን ገልጸው ይህ አጋርነት በዘርፉ የበለጠ መተማመን ይገነባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ህትመቶቹ ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ለባለድርሻ እና ለለጋሽ አካላት የሚሰራጭ ነው ፡፡