የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በልማትና በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የህዝብን የላቀ ተጠቃሚነት የሚረጋግጥ ተግባር መፈጸም እንደሚገባቸው ተጠቆመ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 አንቀጽ 85 መሰረት በሁሉም ድርጅቶች ሙሉ ተሳትፎ የሚመራ ም/ቤት እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡ በዚሁ መሰረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት 4ኛ ጠቅላላ ጉባኤ አካሄዷል፡፡
በጉባኤው ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የባለስልጣኑ ም/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ እንደተናገሩት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት ዓመታት በህግ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሟላ መንገድ ለመተግበር ብርቱ ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥሮላቸው ህግና ስርዓትን በተከተለ መልኩ አገርና ህዝብን በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረግ እንዲችሉ ተደርጓል ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም ባለስልጣን መስሪያቤቱ ባካሄደው ተከታታይ ተቋማዊ ሪፎርም ውጤቶችን በማስመዝገብ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ያለው ተቋም መገንባት መቻሉን በመግለጽ ዝርዝር የአፈፃፀም መመሪያዎች፣ ማኑዋሎች፣ ስታንዳርዶች በማውጣት የአሰራር ስርዓት መዘርጋት፤ በኦንላይ ጭምር ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት፤ ቀላልና ቀልጣፋ የምዝገባ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ፤ እያደገ የሄደ የድጋፍ እና የክትትል አቅም መገንባት፤ ከፌዴራልና ከክልል ባለድርሻ አካላት ጋር ቋሚና ጠንካራ ግንኙነት መፍጠር፤ እንደ ቮለንተሪዝም ማኔጅመንት ኢንፎርሜሽን ሲስተም የመሳሰሉ በጎ ፈቃደኝነትን ተቋማዊ ለማድረግ የሚያስችሉ ወሳኝ ተግባራትን ማከናዎን መቻሉን አንስተዋል፡፡
ሌላው ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ሪፎርም ውስጥ እንደ አንዱ ዋነኛ ስኬት የሚቆጠረው ጉዳይ በአዋጁ የተደነገገው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት በማቋቋም ወደ ስራ መግባት መቻሉ ነው፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ሁሉንም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እንደ ጥላ የሚያሰባስብና የሚወክል ከመሆኑ ባሻገር በዘርፉ የእርስ በእርስ የቁጥጥር ስርዓት እንዲገነባ በማድረግ የዘርፉን መልካም ስምና ተቀባይነት ከፍ የሚያደርግ ወሳኝ ተቋም ነው በማለት ይህ ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ ሊገነባ ከሚፈለገው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ማለትም ህግን አክብሮ፤ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ፤ ከማንም በላይ ለህሊናውና ለመርህ ታማኝ ሆኖ፤ ለህዝብ ጥቅም ወግኖ፤ የአገራዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጣ ተግባር የሚያከናውን የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ መገንባት ከፍተኛ ሚና የሚኖረው ስትራቴጅያዊ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ም/ዋና ዳይሬክተሩ አጽዕኖት ሰተው የተናገሩት ባለስልጣን መስያቤቱ ለምክር ቤቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም ምክር ቤቱም በአዋጅ የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት በተለይም የራስ በራስ ቁጥጥር ስርዓትን በማጠናከር ህግን አክብሮ የሚንቀሳቀስ፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያሰፈነ፣ መልካም ስም ያተረፈ እና ለህዝብ ጥቅም የሚሰሩ ሲማድ መገንባት ላይ ትኩረት አድርጎ ውጤታማ ስራ ማከናዎን ይኖርበታል ብለዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ም/ቤት ለጉባኤው ያከናወናቸውን ስራዎች በ ሪፖርት ለማቅረብ ችሏል፡፡