ከOHCHR እና ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል (Ethiopian human right defenders centre) ጋር በመተባበር በዲጂታል ሴኩሪቲ እና ሰብዓዊ መብት ላይ ስልጠና ተሰጠ፡፡


     

አክለውም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣንን መደገፍ ዘርፉን መደገፍ እንደሆነ የጠቀሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ባለስልጣኑ የጀመረውን ሪፎርም በተሻለ መንገድ መምራት እንዲችል አቅሙን ማሳደግና በአዳዲስ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ልምምድ ማድረግ እንዲሁም የዘመኑን ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና አገልግሎታችንን ዲጂታላይዝ በማድረግ  በአገልግሎታችን ተደራሽ መሆን ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ዘርፍ ከኋላ የሚከተል ሳይሆን አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ከፊት ሆኖ ሀገርን የተሻለ ቦታ ላይ ለማድረስ አስተዋጽዖ ማድረግ መቻል አለበት ያሉ ሲሆን ይህ ስልጠናም በተለይ ከዲጂታል ሴኩሪቲ ጋር በተያያዘ  ያለንን ግንዛቤ ለማሳደግ ትልቅ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በዲጂታል ሴኩሪቲና ሰብዓዊ መብት ላይ ያተኮረ ስልጠና በተለይም በሰብዓዊ መብት ላይ ለሚሰሩ ሀገር በቀል ድርጅቶች ተሰጠ፡፡ ስልጠናው የተዘጋጀው በተመባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ምብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል (Ethiopian human right defenders centre) ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በመተባበር ነው፡፡

የስልጠናው መክፈቻ ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን የOHCHR በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ የሆኑት ቻርለስ ኩዌሞይ (Charlese Kwemoi) ተገኝተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል (Ethiopian human right defenders centre) ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ኃ/ማሪያም በቪዲዮ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ባስተላለፉት መልዕክት በአሁኑ ጊዜ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በተሻለ መንገድ መንቀሳቀስ የሚችሉበት አውድ መፈጠሩን አንስተው ከዚህ የበለጠ አቅም ኖሯቸው ለሀገር ልማትና እድገት የበለጠ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ በተለይም በሀገር በቀል ድርጅቶች ላይ የአቅም ውስንነት መኖሩን ያነሱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ይህን የአቅም ውስንነት በመቅረፍ  ለሀገር የሚጠቅም ውጤታማ ስራ ሊሰሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል (Ethiopian human right defenders centre) ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያሬድ ኃ/ማርያም በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት በሁለት አመት ውስጥ ከ650 በላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በዲጂታል ሴኩሪቲ እና በሰብዓዊ መብት ላይ ስልጠና የተሰጠ  መሆኑን አንስተው ስልጠናው በሰብዓዊ መብት ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች ከሰብዓዊ መብት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ደህንነት መጠበቅ የሚችሉበትን ክህሎት የምናስጨብጥበት ነው ብለዋል፡፡ አክለውም ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር በትብብር ስልጠናውን ማዘጋጀት በመቻላቸው ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በሌሎች በርካታ ስራዎች ላይ በጋራ እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡

የOHCHR በኢትዮጵያ ምክትል ተወካይ የሆኑት ቻርለስ ኩዌሞይ (Charlese Kwemoi) በበኩላቸው የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ የሰብዓዊ መብቶች ላይ ቅስቀሳ ለማድረግ እና ተግባራዊ ለማድረግ እድል መፍጠሩን አንስተው እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በአግባቡ ደህንነታቸው ተጠብቆ በኃላፊነት ካልተጠቀምንባቸው ለሌላ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ሊያጋልጡ እንደሚችሉ አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰብዓዊ መብቶች ላይ ቅስቀሳ የሚያደርጉት እነዚህን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቅመው መሆኑን ያነሱት ሚስተር ቻርለስ ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆናቸው ባሻገር በዚያው ልክ ለአደጋ የሚያጋልጡ በመሆናቸው ደህንነታቸውን መጠበቅ እና በየጊዜው የደህንነት መጠበቂያ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ ስልጠናው ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተሰጠ ሲሆን በሰብዓዊ መብት ላይ ከሚሰሩ የተለያዩ ሀገር በቀል ድርጅቶች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ስልጠናውን ውስደዋል፡፡