ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር ተካሄደ::
ላለፉት ሁለት ዓመታት በሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች በተደረገው ጦርነት በትግራይ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ይታወቃል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ በመስጠት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት በሰላም እንዲፈታ አድርጓል፡፡ በሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር ላይ የተገኙት የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ አለም አንተ አግደው ባደረጉ ንግግር ለትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍ እና መልሶ ማቋቋም መርሀ ግብር ላይ ለተገኙ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ምስጋናቸውን በማቅረብ መንግስት በአገራችን ግጭትና ጦርነት ቁሞ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እና ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠቃሚ ወደሆነው ወደልማትና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ሙሉ በሙሉ ማተኮር እንዲቻል ለሰላም አማራጭ ቅድሚያ በመስጠት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተከስቶ የነበረውን ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት በሰላም እንዲፈታ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም በሀገራችን ሲንከባለሉ የመጡ ቁርሾዎች፣በደሎች፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እውነትን በማፈላለግ በተጠያቂነት፣ በእርቅና በይቅርታ ለመዝጋት የተጀመሩ የሀገር ግንባታ ስራ በጣም ወሳኝ መሆኑ መንግስት በጽኑ እንደሚያምን በማመላከት መንግስት ገለልተኛ የሆነ ብሔራዊ የምክክር ኮሚሽን በማቋቋም በአገራችን የግጭት፣ የጦርነት፣ የቁርሾና ያለመግባባት መንስሄዎችን በዳበረ ውይይትና ምክክር ለመፍታት ሰፊ እቅስቃሴዎች እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው ሌላው ያነሱት ጉዳይ ከሀገራዊ ለውጡ በኋላ የተሻለ የፖሊሲ፣ የህግና የተቋማት ሪፎርም ተካሄዶ ለመንቀሳቀስ ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸው የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች በአገራችን ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና በመንግስ በኩል የተጀመሩ እቅስቃሴዎች እንዲሳኩና እንዲተገብሩ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በተካሄደው ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ወገኖቻችን ከፍተኛ ችግር ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ በአሁን ወቅት የሁላችንም ድጋፍ ይሻሉ በማለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ በክልሉ መልሶ ግንባታና ማቋቋም ሂደት የሚያደርጉት ሁነኛ አስተዋጽኦ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ግጭቶች እንዲወገዱ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ እዲፈቱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ እንዲሁም የሰላም ጠቀሜታና አስፈላጊነት ዙሪያ ከፍተኛ ሚና ያላቸው በመሆኑ ስራቸውን አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደተናገሩት ለአንድ አገር እድገትና ለህዝቦች ኑሮ መሻሻል ትልቁን ሚና የሚጫወተው ሰላም መሆኑን ከኛ በላይ ምስክር የለም በማለት ያለሰላም ልማትም ሆነ እድገት ዴሞክራሲም ሆነ አገር የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ገልፀዋል፡፡
አያይዘውም የሰላም ስምምነቱ የመሳሪያ ግጭትን ያስቆመ ቢሆንም በጦርነት ምክንያት የደረሱ ጉዳቶችና በህብረተሰቡ የደረሱ የስነልቦና ጫናዎች በአግባቡ መታካም እንዳለባቸው በማንሳት የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና አለባቸው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ በትግራይ ክልል ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከመሀል አገር ካሉ የሲቪልማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በከፍተኛ አገራዊ ስሜት የችግሩን ጥልቀት በመለየት ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በአፋጣኝ ድጋፍ የሚደረግበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ለወገን ደራሽ ወገን እንደሚባለው በችግር ላይ የሚገኝን የማህበረሰብ ክፍል ከማገዝ የሚበልጥ ሰብዓዊ ተግባር የሌለ በመሆኑ ይህ አስቸጋሪ ወቅት በመተጋገዝ የወገን አሌንታችንን ማሳየት አለብን በማለት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እስካሁን ሲያደርጉት ለነበረው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ በተካደው መርሀ ግብር ላይ የባለስልጣኑ ም/ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በባለስልጣኑ የተከናወኑ የሰብዓዊ ድጋፎች በተመለከተ ማብራሪ ያቀረቡ ሲሆን ከትግራይ የተወከሉ ባለሙያ በክልሉ ስላለው ጉዳትና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስለሚጠበቅ ጉዳይ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በመድረኩም 29 ሚሊየን ብር የሚገመት የዓይነትና የብር ድጋፍ የተገኘ ሲሆን ሌሎች ተሳታፊ ድርጅቶቹ በወሰዱት ፕሌጅ መሰረት ከሃላፊዎቻቸው ጋር በመነጋገር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡