የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ለልማትና ለዲሞክራሲ ማበብ ወሳኝ ሚና እንዳላቸው ተገለጸ።

የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማእከልና ከደቡብ አመራር አካዳሚ ጋር በመተባበር ለዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ያዘጋጀው ስልጠናና የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሄደ ነው። የኢፌዲሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት የልማት ሰላምና ዴሞክራሲ የተረጋገጠባት አገር ለመገንባት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከፍተኛ ሚና አላቸው። በዚህም መንግስት ለዘርፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ያመለከቱት ሃላፊው የመንግስት ድጋፋዊ ክትትል እያደረገ በመምጣቱም ዘርፉ እየተነቃቃ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የመደራጀት መብት በመረጋገጡ ማህበራት የተሻለ ጥረት እያደረጉ ናቸው ያሉት አቶ ፋሲካው፣ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከ45ሺህ በላይ የምርጫ ታዛቢዎችን በመመደብ የምርጫ ሂደቱን እንዲታዘቡ ማድረጋቸው የዚህ ማሳያና አንዱ ስኬት ነው ብለዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አጋርነታቸውንና ትብብራቸውን በማጠናከር አገራችን የጀመረችውን የብልጽግና ጉዞ እንዲሳካ መረባረብ እንዳለባቸውም አቶ ፋሲካው ሞላ ገልጸዋል። የደቡብ ክልል የዴሞክራሲ ግንባታ ማስተባበሪያ ማእከል የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት ዘርፍ ሃላፊ ወይዘሮ ጸዳለች ሚካኤል በበኩላቸው ማህበራቱ በመንግስትና በህዝብ መካከል ድልድይ በመሆን ብልጽግናን በማረጋገጥ እና የህብረተሰቡን የልማት ተጠቃሚነትን በማሳደግ ረገድ የድርሻቸውን መወጣት ይገባቸዋል ብለዋል።
ሲቪል ማህበራት በርከት ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የሚያሳትፉ በመሆናቸው የበለጸገችና ጠንካራ አገር ለመገንባት የሚደረገውን ሁሉ አቀፍ ጥረት እንዲያግዙም ጠይቀዋል። ማህበራቱ ሁሉ አቀፍ ብልጽግና እንዲረጋገጥ የማይተካ ሚናቸውን እንዲወጡ ወይዘሮ ጸዳለች አሳስበው ሀገር በጠንካራ መሰረት ላይ እንድትቆም በሚያደርግ ጉዳይ ላይ ምቹ ሁኔታ በመኖሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። የደቡብ አመራር አካዳሚ ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብዱልበር ኡስማን በበኩላቸው አካዳሚው መንግስታዊና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶችና የሲቪክ ተቋማት ለችግሮች መፍትሄ የሚሰጥና ጥራት ያለውን ሥልጠና እንዲሁም የማማከርና የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እያከናወነ መቆየቱን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህም አካዳሚው ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር አብሮ እንደሚሰራ እና አስፈላጊውን የአቅም ግንባታ ስራዎችን በማከናወን የጀመራቸውን የምርምርና የማማከር ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አሳውቀዋል። ስልጠናውና የምክክር መድረኩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አካዳሚው አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉንም ያነሱት አቶ አብዱልበር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የህዝብ ማህበራዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች እንዲመለሱ የጎላ ሚና እንዳላቸውም አመልክተዋል። የስልጠናና የውይይት መድረኩ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚካሄድም ታውቋል።
ምንጭ፡- ደቡብ አመራር አካዳሚ