በአእምሮ ህመም ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች ህብረት መመስረት እንዳለባቸው ተገለጸ፡፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በአእምሮ ህሙማን ላይ የሚሰራውን ቦርን አጌን ሜንታልኸልዝ ሪሀብሊቴሽን ኤንድ ሂሊንግ የበጎ አድራጎት ድርጅትን ጎብኝተዋል፡፡
በንግድ ስራ ይተዳደሩ የነበሩት ወ/ሮ ኪያ ስብሃት በህይወት አጋጣሚ ያገኟትን የእእምሮ ታማሚ በማንሳት ነበር የበጎ አድራጎት ስራን የጀመሩት፡፡ አንድ ሰው በማንሳት የተጀመረው ይህ መልካም ሀሳብ እያደገ መጥቶ በ2008 ዓ.ም በቀድሞው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ በአሁኑ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተመዝግቦ “ቦርን አጌን ሜንታል ኸልዝ ሪሀብሊቴሽን ኤንድ ሂሊንግ የበጎ አድራጎት ድርጅት” በሚል ስያሜ ህጋዊ ሰውነት ያለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ወደ መሆን ተሸጋገረ፡፡
“በአእምሮ ህመም ምክንያት አንድም ሰው በጎዳና ላይ አያድርም” የሚል መርህ አንግቦ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ቦርን አጌን ሜንታል ኸልዝ ሪሀብሊቴሽን ኤንድ ሂሊንግ የበጎ አድራጎት ድርጅት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ከ374 በላይ የእዕምሮ ህሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት ከአእምሮ ህመማቸው እንዲያገግሙ አድርጓል፡፡ በአሁን ጊዜም ከ122 በላይ የአእምሮ ህሙማንን በመደገፍ ላይ የሚገኝ ሲሆን 23 የሴት የአእምሮ ህሙማን ልጆችንም በማሳደግ ላይ ይገኛል፡፡
የዚህን ሀገር በቀል ድርጅት የስራ እንቅስቃሴ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እና የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስራ ኃላፊዎች በቦታው ተገኝተው ጎብኝተዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ድርጅቱ ምንም ቋሚ የገቢ ምንጭ ሳይኖረው በኪራይ ቤት ሆኖ ይህን ትልቅ ስራ መስራት በመቻሉ ምስጋናቸውን አቅርበው ድርጅቱ የበለጠ ውጤታማ ስራ መስራት እንዲችል ከተለያዩ ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለበት አንስተዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ከሚመለከታቸው ተቋማትና በጎ ፈቃደኞች ጋር መስራት ድርጅቱ ያለበትን ችግር በመጠኑም ቢሆን እንደሚቀንስለት አንስተዋል፡፡
በአእምሮ ህመም ላይ የሚሰሩ ድርጅቶች በጋራ በመሆን ህብረት መመስረት ቢችሉ ያለውን ውስን ሀብት በጋራ በመጠቀም የተሻለ እገዛ ማድረግ እና የበለጠ ተደራሽ መሆን አንደሚችሉ አጽንዖት ሰጥተው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ የአእምሮ ህመም ችግር ተመሳሳይ በመሆኑ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የምታውቁ እንዴት መረዳዳት እንዳለባችሁ መነጋገር መቻል ያለባችሁ በመሆኑ በአእምሮ ህሙማን ላይ የምትሰሩ ድርጅቶች ተሰባስባችሁ ህብረት ብትመሰርቱ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከአእምሮ ህመም ያገገሙ ዜጎች ተሰባስበው ማህበር መመስረት ቢችሉ ስለጉዳዩ በቂ ግንዛቤ ስላላቸው የተሻለ ስራ መስራት የሚችሉበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡ ድርጅቱ በገቢ ማስገኛ ስራዎች ላይ የሚሳተፍበትን መንገድ መመልከት ቢችል በገቢ በኩል ያለበትን ችግር ከመቅረፍ ባለፈ ከአእምሮ ህመም ለሚያገግሙትም የስራ እድል የሚፈጥር ይሆናል ብለዋል፡፡
አንድ ሰው ከጎዳና ላይ በማንሳት የተቋቋመው ይህ ቦርን አጌን ሜንታል ኸልዝ ሪሀብሊቴሽን ኤንድ ሂሊንግ የበጎ አድራጎት ድርጅት የተባለው ሀገር በቀል የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት 23 ሰራተኞች ያሉት ሲሆን ከነዚህ ውስጥ 22 የሚሆኑት የድርጅቱ ሰራተኞች በድርጅቱ ከአእምሮ ህመም በማገገም ወደስራ የገቡ እንደሆነ የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ የሆኑት ወ/ሮ ኪያ ስብሃት ገልጸውልናል፡፡
Click the button