ታላቁ የህዳሴ ግድብ የኢትዩጵያ የአንድነት አርማ ምልክት ነው::

ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የጎላ ተሳትፎ በማድረግ ታሪካዊ አሻራችንን እናሳርፍ በሚል መሪ ቃል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉብኝት ተደርጓል፡፡ በጉብኝቱ የተቋሙ ከፍተኛ ሃላፊዎች ጨምሮ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አመራሮች እንዲሁም የህዳሴ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሃላፊዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ በጉብኝቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያቤቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ሲገልጹ ግድቡን ለመጎብኘት ሲታቀድ ሁለት ዓላማዎች አሉት የመጀመሪያው ለዓመታት ግድቡን በመስራት ላይ ያሉትን አመራሮችና ሰራተኞች ለማመስገን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ አሻራቸውን እያሳረፉ መሆናቸውን እና በቀጣይ በምን መልኩ ማገዝ እንዳለባቸው ለማወቅና ከአመራሩ ጋር ለመወያየት ነው ሲሉ አንስተዋል፡፡ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ግድቡ እዚህ ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በአገር ደረጃም ግድቡ የኔ ነው በማለት ከፍተኛ የንቅናቄ ስራዎች መስራታቸው እንዲሁም በአገር አቀፍ ደረጃ መድረኮችን በማዘጋጀት ትልቅ ሚና መጫወታቸውን ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው አጽእኖት ሰተው የተናገሩት ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግድብነት ያለፈ ትርጉም እንዳለው በማንሳት የኢትዮጵያ የአንድነት አርማ፣ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚያስተሳስራቸው ገመድ እንዲሁም የአገራችን የመልማትና የማድግ ተስፋ የሚሰጥ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም ታላቁን የህዳሴ ግድብ ከፍጻሜ ማድረስ በብዙ መልኩ ትልቅ ትርጉም እንዳልው በመገንዘብ በቀጣይም ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል፡፡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ አጠቃላይ ስለግድቡ ሰፊ ማብራሪያ በማድረግ ባስተላለፉት መልዕክት ይህ ግድብ ባለቤቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ነው በማለት አገራችን በብዙ ችግሮች ውስጥ ሆናም የግድቡ ስራ ለአንድ አፍታም ሳይቋረጥ የቀጠለ መሆኑን ገልፀው ይህ የሆነው የመንግስት ቁርጠኝነትና የህዝቡ ድጋፍ ስላልተለየው ነው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ግድቡ ከፍጻሜ እንዲደርስ እጅ ለእጅ በመያያዝ በጋራ ከግብ ማድረስ አለብን ብለዋል፡: በመጨረሻም ተቋሙ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ቀን ከሌሊት ለሚሰሩ አመራሮችና ሰራተኞች የሰርተፍኬት በማዘጋጀት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን አክሽን ፎር ዘ ኒዲ የተባለ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅትም የሶስት መቶ ሺህ ብር ቼክ ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ማስተባባሪያ ጽ/ቤት አስረክቧል፡፡