የትግራይ ክልልን መልሶ በማቋቋም ሂደት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ ይደረጋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ ገለጹ፡፡

ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በAssociation of CSOs in Tigray አስተባባነት በትግራይ ክልል ከሚገኙ የሲቪል ማህረሰብ ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱ 90 በመቶ የሚሆነው የማህበረሰብ ክፍል የሰብዓዊ እርዳታ ተጠቃሚ መሆኑን እና ከ2ሚሊየን በላይ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በክልሉ እንደሚገኙ ተገልጷል፡፡
Association of CSOs in Tigray ኤክስክዩቲቭ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ በትግራይ ክልል ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ሲያብራሩ ሲማዶች ጦርነቱ እንዲቆምና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ገልጸው በክልሉ ያሉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ወደቀደመው ስራቸው እንዲመለሱ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን እና ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት አፋጣኝ ድጋፍ እንደሚሹ ገልጸዋል፡፡
በውይይቱ በተነሱ ርዕሰ ጉዳዬች ላይ ምላሽ የሰጡት ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ እንደገለጹት በጦርነቱ ምክንያት ሪፖርት ባላቀረቡ ድርጅቶች ላይ የስረዛ ውሳኔ አለመውሰዱ እና በቂ ጊዜ አግኝተው የሚጠበቅባቸውን እንዲያደርጉ ሁኔታዎች እየተመቻቹ ስለመሆኑ፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የባንክ ሂሳብ መክፈት እና የፈራሚ ለውጦች መደረጉ፤በክልሉ ለሚገኙ ሲማዶች በአዋጅና መመሪያዎች ላይ በቅርቡ ስልጠና እንደሚሰጥ፤ተቋሙ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ እና በክልሉ ሰፋፊ የውይይት መድረኮች እንደሚዘጋጁ እና በአጠቃላይ ክልሉን መልሶ በማቋቋም ሂደት ሲማዶች የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ አስፈላጊ ድጋፍ ሁሉ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደር ም/ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ በበኩላቸው ሲማዶች የሰላም ስምምነቱ ዘላቂ እንዲሆን እና የሽግግር ፍትሁ ውጤታማነት ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸው ሕዝቡ ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጠ በመሆኑ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም በመቀሌ ቅርብ ርቀት በሚገኘው ሰባካ የስደተኞች ካምፕና በመቀሌ ከተማ ዐዲ ሃቂ ት/ቤት ውስጥ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች /IDPs/ በአካል በመገኘት ተመልክተዋል፡፡