ስታንድ ፎር ቨልነረብል (Stand for vulnerable organization) የተባለ ሀገር በቀል ድርጅት በገቢ ማስገኛ ላይ የሰራቸውን ስራዎች ለባለስልጣኑ የስራ ኃላፊዎች አስጎበኘ፡፡

በፕሮግራሙ የአንቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹን ጨምሮ በርካታ የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡ በባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ የተመራው ልዑክ በቡራዩ እና አንቦ ከተማ ድርጅቱ ያከናወናቸውን የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች ተመልክቷል፡፡
የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ምስጋናው ድርጅቱ ዓላማ አድርጎ የሚሰራው በተለያዩ አካባቢዎች ወላጅ አልባ ህጻናትን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ ማሳደግ እና ሴቶችን በኢኮኖሚ እንዲበቁ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረግ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ አክለውም የድርጅቱን ቀጣይነት ለማረጋገጥ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011 በፈቀደው መሰረት ኤግል የሚል የንግድ ስያሜ በማውጣት የገቢ ማስገኛ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡
በጉብኝቱ ላይ የተገኙት የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃጫሉ ገመቹ በንግግራቸው እንዳሉት ድርጅቱ በከተማው ሴቶችና ህፃናት ላይ ትርጉም ያለው ስራ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ እንደከተማ አስተዳደር በተቻለ መጠን ድጋፍ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም በገቢ ማስገኛነት እየሰሯቸው ያሉ ስራዎች ማህበረሰቡን ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ማስቻሉን እና ለበርካታ ሴቶች የስራ ዕድል በመፍጠር ትልቅ ሚና መጫወታቸውንም አያይዘው ገልጸዋል ፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድረጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ በጉብኝቱ ማጠቃለያ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ ከተቋቋመ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ መሆኑን በማስታወስ ይህ ሆኖም በፅናት የማህበረሰቡን የልማት ተጠቃሚነት በማስቀጠል ዛሬ መድረሱ ያለውን ጥንካሬ ያሳያል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ አሁንም በገቢ ማስገኛ የሰሯቸው ስራዎች ለበርካታ የስራ አጥ ዜጎች የስራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ ለተሰማራበት የበጎ አድራጎት ስራ ከፈንድ ጠባቂነት በማላቀቅ በራሱ መቆም እንዲችል ያደርገዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡